ቀጥታ፡

በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)

ቦንጋ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት በሰላም፣በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

የክልሉ የ2018 ዓ.ም የሶስት ወራት የፓርቲና መንግስት ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው ።


 

የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር  ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት ባለፉት ሶስት ወራት የፓርቲና የመንግስት ስራዎች በተናበበ መልኩ ሲከናወን ቆይቷል።

ለተግባራዊነቱም የአመራሩንና የሰራተኛውን አቅም በመገንባት የመንግስት አገልግሎቶችን ለማሳለጥ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።

በዚህም የክልሉን  ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ውጤታማ ማድረግ መቻሉን  ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

በተለይም በትምህርት፣ በጤናና  የግብርናው ዘርፍ  ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ጠቁመዋል።

የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ተግባራትም በመኸር እርሻ 350 ሺህ ሄክታር መሬት በዋናዋና ሰብሎች በመሸፈን ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።


 

የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ለማሳካት የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች ወደ ስራ መግባታቸውንና  የሻይ ልማትን በማስፋት  የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ  መሰራቱን  ጠቁመዋል።

እነዚህን የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት  የድጋፍና ክትትል ስራዎች እንደሚጠናከሩ  ተናግረዋል።

ለአንድ ቀን በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ የፓርቲና የመንግስት የሶስት ወራት የስራ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም