ቀጥታ፡

የንግዱ ማሕበረሰብ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የተፈጠረውን የገበያ ዕድል አሟጦ ለመጠቀም ዝግጅት ማድረግ አለበት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ የንግዱ ማሕበረሰብ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የተፈጠረውን የገበያ ዕድል አሟጦ ለመጠቀም ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዴስክ አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ግዛው፤ የአፍሪካ  አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና  ግብይት  ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውሰዋል።


 

ግብይቱ  በአፍሪካ ካለው ሰፊ የሕዝብ ቁጥርና አመታዊ ምርት /ጂ.ዲ.ፒ/አንፃር ሰፊ የገበያ እድል ይዞ የመጣ በመሆኑ የንግዱ ማሕበረሰብ እና ሌሎች ተዋንያን በስፋት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ግብይቱ በዋናነት ታሪፍን ከመቀነስ ባለፈ አስቸጋሪ የሆኑ አሰራሮችን የሚያስቀር በመሆኑ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

ግብይቱ የወጭ ንግድ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ፍጥነት የሚያሳድገው በመሆኑ መንግስት መደላድሎችን መፍጠሩን ነው  አቶ ሳሙኤል  የገለጹት።

የንግዱ ማሕበረሰብ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የተፈጠረውን የገበያ እድል አሟጦ ለመጠቀም ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት።

የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ስራ ላይ መዋሉ የመዳረሻ ሀገራትን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ገልፀዋል።

ስምምነቱ ምርቶችን ወደ አፍሪካ ሀገራት ገበያዎች ለመላክና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ አምራቶችና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ከሊፋ ሁሴን እንዳሉት፤አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው መጀመሩ በአፍሪካ ሀገራት ትልቅ የገበያ እድል ለማግኘት የሚያስችል  ነው።


 

እስካሁን ባለው ሒደት የኢትዮጵያ ስጋ የሚላከው በአብዛኛው ወደ ሩቅ ምስራቅ ሀገራት ሲሆን ስምምነቱ መፈረሙ ይሕንን በእጅጉ የሚያሳድገው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የስጋ ምርት ፍላጎት ያለ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው፤ ላኪዎችን ከማበረታታት ባለፈ የሀገርን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እንደሆነም ገልፀዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚደርስባቸው የአፍሪካ ሀገራት የተሳለጠ የንግድ ግንኙነት ለማድረግ የሚረዳ  መሆኑን  አብራርተዋል።

ከታሪፍ አኳያ ተወዳዳሪ ለመሆን ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን የሚያስቀሩ እድሎችን ይዞ መምጣቱንም ነው የገለጹት። 

የኢትዮጵያ አበባና አትክልት አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ  አህጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ተግባራዊ መድረጉ የወጪ ንግድ መዳረሻን ለማስፋት የሚያግዝ ነው፡፡


 

ይህም ኢትዮጵያ ምርቶቿን በብዛት ወደ ውጭ በመላክ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ የሚያስችላት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዋናነትም ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ትልቅ እድል ይዞ የመጣ መሆኑንም ነው የገለጹት።

መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጣና ግብይት መጀመሩ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም