ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል ስኬት የተመዘገበበት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ለማድረግ በተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራዎች ለተሳተፉ አካላት የምስጋና መርሀ ግብር ተከናውኗል።


 

ከመስቀል አደባባይ መገናኛ ሳውዝጌት፣ ከቦሌ ቪ አይ ፒ ጎሮ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ ከአንበሳ ጋራዥ ጎሮ እና ከሳር ቤት ጀርመን አደባባይ ሀይሌ ጋርመንት ፉሪ አስደማሚ ስራ እንዲከናወን ላደረጉት የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ ኢንጂነሮች፣ አማካሪዎች፣ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ተመስግነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ለከተማዋ ልማትና ውበት ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል።

በአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት የተመዘገበው ውጤት መዲናዋ የብልጽግና ተምሳሌትነቷን በተሟላ ሁኔታ መተግበር የሚያስችላትን አቅም መገንባቷን ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለሀገር ብልጽግና መሰረት የሚጥል ስኬት እየተመዘገበበት መሆኑንም አንስተዋል።


 

ለዚህ ስኬት ደግሞ ከገንዘብ ይልቅ የህዝባቸውንና ሀገራቸውን መልማት አስቀድመው ስራውን በፍጥነትና በጥራት እንዲሰራ ላደረጉ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ የተለያዩ ማህበራትና በጎ ፈቃደኞች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያን በማልማት ወደምንፈልገው ብልጽግና ለመሸጋገር ትብብር ትልቅ መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ መተባበርና መሰባሰብ የተጀመረውን የብልጽግና ራዕይ ዕውን ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

ከአዲስ አበባ ስፋትና ከሚገባት አንፃር ትብብሩ ከዚህ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።


 

የአዲስ አበባን ገጽታ መቀየር ትልቅ ትርጉም እንዳለው ጠቁመውም መዲናዋ የኢትዮጵያ መታያ፣ መለኪያና ነፀብራቅ መሆኗን ያሳያል ብለዋል።

የመዲናዋ የኮሪደር ልማት በሌሎች ክልሎች ለተጀመሩ ስራዎች ልምድ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ ስኬቱ ለትውልድ የሚተርፍ ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ለበርካታ ዜጎችና ማህበራት የስራ ዕድል የፈጠረ፣ ዋነኛ የመዝናኛ ስፍራ የሆነ፣ አዲስ አበባ ስማርት ሲቲ መሆኗ በተግባር የተገለጠበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም