ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ነገ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ይሰጣሉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በነገው ዕለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ይሰጣሉ።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ነገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል።

በዚህ መደበኛ ስብሰባ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡

ይህን ተከትሎም ምክር ቤቱ የመንግሥትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዕለቱ በሚካሄደው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ተጠሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

የስብሰባው ሙሉ ሂደትም በቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ እንደሚተላለፍ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም