ቀጥታ፡

የኮይሻ የኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኃይል ፍሰት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፦1800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ የኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኃይል ፍሰት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ በአመት 6,344 ጊጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ሲልም አስታውቋል።


 

ጽህፈት ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣም መልዕክት የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በኦሞ ወንዝ ታችኛው ተፋሰስ ከጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ 129 ኪሎ ሜትር ርቀት ከኮይሻ መንደር በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል ብሏል።

1800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ የኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኃይል ፍሰት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ነው ሲልም ገልጿል።


 

ከኃይል አቅርቦት ማስፋፊያነቱ ባሻገር የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ንፁህ፣ አስተማማኝ እና የተጠቃሚዎችን አቅምን ከግምት ያስገባ ታዳሽ ኃይል አቅርቦት የሚያቀርብ ኢትዮጵያም በምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ የውጭ ንግድ ማዕከል ለመሆን ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሳካት የሚደግፍ ነው ብሏል።

በሀገር ውስጥም የገጠር ኤሌክትሪክ አቅርቦትን በሚደግፍ መንገድ በመኖሪያ ቤቶች እና በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ያሳድጋል ነው ያለው።


 

ይኽም ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚያነቃቃ፣ የተሻሻለ የአኗኗር ደረጃን የሚፈጥር ብሎም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዘላቂ እድገትን የሚደግፍ እንደሚሆን ይጠበቃል ሲልም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም