ቀጥታ፡

የብዙዎች ቤት…

እስካሁን በተደረገ የጥናት ውጤት መሠረት ከ81 በላይ የአጥቢ እንስሣት፣ ከ450 በላይ የአዕዋፍ እና ከ400 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች መኖሪያ ነው።

ከእነዚህ መካከል አምስቱ የአዕዋፍ ዝርያዎች በዚህ ሥፍራ ብቻ ይገኛሉ፤ ከአምስቱ መካከል በተለይም የአንዷ ዝርያ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተመራማሪዎችንና ጎብኚዎች ቀልብ መሳቡ ይጠቀሳል።

ከአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥና የአየር ሁኔታ ጋር መጣጣም የቻሉ የቆላ እፅዋት (ዛፎች) በምቾት በስፋት እንደሚገኙበትም ይገለጻል።

የተመሠረተው በ1958 ዓ.ም ሲሆን፤ ስፉቱም 591 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፤ በቁጥርም ሆነ በሥብጥር የብዙዎች መኖሪያ የሆነው ይህ ሥፍራ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ይሰኛል።

መንግሥት በሰጠው ትኩረት ከነበረው በተሻለ ሁኔታ እንስሣቱም ሆኑ እፅዋቱ እየኖሩ ነው፤ ከሕገ ወጥ ድርጊትም እንዲጠበቁ ማድረግ መቻሉን የፓርኩ ኃላፊ አደም መሐመድ ለኢዜአ አረጋግጠዋል።

በፓርኩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁንም ለ247 ወገኖች ቋሚ እና ለ2 ሺህ 535 ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ዓመትም በ1 ሺህ 751 የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እንደተጎበኘ ኃላፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም