ቀጥታ፡

የጭንቀት መንስዔዎች እና የሕክምና መንገዶቹ !

የአዕምሮ ህመም እንደ ድባቴ እና በጭንቀት መታወክን ጨምሮ ከሱስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ህመሞችን እንደሚያካትት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ኢማኑኤል አሥራት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታም፤ የጭንቀት መንስዔ፣ ምልክቶች እና ሕክምናውን አስመልክቶ ሙያዊ ገለጻ አድርገዋል።

የጭንቀት መንስዔዎች

ዶክተር ኢማኑኤል እንዳሉት፤ ጭንቀት አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በሥነ-ሕይወታዊ (አንጎል ውስጥ ባሉ ንጥረ-ነገሮች መዛባት)፣ ሥነ-ልቦናዊ እና አካባቢያዊ (ማኅበራዊ) ሁኔታዎች መሥተጋብር ነው።

👉 ሥነ-ሕይወታዊ ተጋላጭነት፡- ጄኔቲክስ (በቤተሰብ የጭንቀት ህመም ያለበት ሰው መኖር)፣ አንጎል ውስጥ ባሉ ንጥረ-ነገሮች መዛባት፣ የአካላዊ ጤንነት እክሎች (የታይሮይድ በሽታ፣ የልብ ምት መዛባት፣ አስም) በዚህ የአጋላጭነት ምድብ ይነሳሉ።

👉 ሥነ-ልቦናዊ ተጋላጭነት፡- አሰቃቂ ወይም አስጨናቂ የሕይወት ተሞክሮዎች (ጾታዊ ጥቃቶች፣ ኪሳራ፣ አደጋዎች)፣ የግለሰባዊ ባሕርይዎች (ፍጹም ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ (Perfectionism) እና ዝቅተኛ በራስ መተማመን) የሚሉት ደግሞ በሥነ-ልቦናዊ ተጋላጭነት ተነስተዋል።

👉 የአካባቢ (ማኅበራዊ) ሁኔታዎች፡- ሥር የሰደደ ውጥረት (የሥራ፣ የገንዘብ፣ የትምህርት ጫና)፣ ዋና ዋና የሕይወት ለውጦች (ስደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ አዲስ ሥራ)፣ የሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች አጠቃቀም (አልኮል፣ ካፌይን፣ መድኃኒቶች) ጭንቀትን ሊያስከትሉ ወይም ሊያባብሱ ይችላሉ ብለዋል ዶክተር ኢማኑኤል።

የጭንቀት ምልክቶች

የጭንቀት ምልክቶች በአብዛኛው በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በባሕርይ እንደሚከፈሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።

📌 አካላዊ ምልክቶች፡- ፈጣን የልብ ምት፣ የትንፋሽ እጥረት፣ ማላብ፣ መንቀጥቀጥ፣ ማዞር፣ ማቅለሽለሽ፣ ራስ ምታት እና የጡንቻ ውጥረት ጭንቀት ከሚያሳያቸው አካላዊ ምልክቶች መካከል ናቸው ይላሉ።

📌 ሥነ-ልቦናዊ ምልክቶች፡- ከመጠን በላይ መጨነቅ (ስለ ዕለታዊ ነገሮች፣ ብዙ ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ስሜት)፣ የፍርሃት ስሜት፣ እየመጣ ያለ ከፍተኛ ጥፋት እንዳለ መሰማት፣ እረፍት ማጣትና ትኩረት የመሰብሰብ ችግር መሆናቸውን ያነሳሉ።

📌 የባሕርይ ምልክቶች፡- ጭንቀት የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን አብዝቶ መፍራትና መሸሽ (Avoidance)፣ ቶሎ መበሳጨት፣ የእንቅልፍ መዛባት (እንቅልፍ ማጣት ወይም እረፍት የሌለው እንቅልፍ) መሆናቸውን አብራርተዋል።

የጭንቀት ሕክምና

ሕክምናው በጭንቀቱ ክብደት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ኢማኑኤል፤ በአብዛኛው ሕክምናን + የአኗኗር ዘይቤን + አንዳንድ ጊዜ መድኃኒቶችን ያጣምራል ይላሉ።

👉 ሳይኮሎጂካል ሕክምናዎች፡- የንግግር ሕክምናዎች ውጤታማ የሕክምና አማራጮች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።

👉 የመድኃኒት ሕክምና፡- ይህ የሕክምና ዓይነት በአጭር ጊዜ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ውጤታማ አማራጭ ነው ይላሉ።

👉 የአኗኗር ዘይቤ እና ራስን መርዳት፡- መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ (የጭንቀት ሆርሞኖችን ይቀንሳል)፣

የተመጣጠነ አመጋገብ (ከመጠን በላይ ካፌይን፣ ስኳር፣ አልኮልን ማስወገድ)፣

ለእንቅልፍ ትኩረት ሰጥቶ በቂ የእረፍት ጊዜን መለየት፣

ማኅበራዊ ድጋፍ (ከጓደኞች፣ ቤተሰብ፣ የድጋፍ ቡድኖች ጋር መነጋገር) የሚሉትን ዘርዝረዋል።

በአጠቃላይ ጭንቀት ሊታከም የሚችል መሆኑን አረጋግጠው፤ በርካቶች በንግግር ሕክምና፣ በመድኃኒት ወይም በሁለቱም ውጤታማ ሕክምና እንደሚያገኙ ማወቅ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም