ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ባልፈለጉ አካላት የተነጠቀችውን የባህር በር መጠየቅ መብቷ እንጂ ቅንጦት አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ባልፈለጉ አካላት የተነጠቀችውን የባህር በር መጠየቅ መብቷ እንጂ ቅንጦት አይደለም
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ባልፈለጉ አካላት የተነጠቀችውን የባህር በር መጠየቅ መብቷ እንጂ ቅንጦት አይደለም ሲሉ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሴ አስገነዘቡ።
ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት ሂደት ሕጋዊ አለመሆኑን አንስተው፤ መንግሥት ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት አምኖ አጀንዳ ማድረጉ ከሕግም ሆነ ከሞራል አንጻር ትክክል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግስት እንደ ባሕር በር ያሉ ቁልፍ ሀገራዊ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ሕጋዊ መብት እንደሌለው እያወቀ፤ ኢትዮጵያን ባሕር በር አልባ ማድረጉን አውስተዋል።
ለዓለምና አኅጉር አቀፍ ትላልቅ ተቋማት ምሥረታ ፊታውራሪዋ፤ ከጎረቤቶቿ ጋርም በሰላም ማስከበር፣ በወንዝ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመሠረተ-ልማት የተቆራኘችው ኢትዮጵያ ከሚናዋ አንጻር የባሕር በር ጥያቄዋ ሊደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ባልፈለጉ አካላት የተነጠቀችውን የባህር በር መጠየቅ መብቷ እንጂ ቅንጦት እንዳልሆነም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ከሞራልም ሆነ ከሕግ አንጻር የተፈጸመው ስህተት መሆኑን አስገንዝበው፤ ኢትዮጵያ በአሻጥር የተቀማችውን የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንድታጠናክር መክረዋል።
ይህ ተሳካ ማለት ጥቅሙ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር መሆኑን በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያ ደኅንነትና መልማት የቀጣናው ጭምር ስለሆነ ጥያቄዋ እንዲመለስ መደገፍ ይገባል ብለዋል።
ከባሕር በር ጋር በተያያዘ ከሳዑዲ ዓረቢያ እና ጆርዳን እንዲሁም ከአንጎላ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተሞክሮዎች መማር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አይቻልም የሚባል ነገር እንደሌለ አመላክተዋል።