በክልሉ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት ለጎብኚዎች መዳረሻ በማድረግ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት ለጎብኚዎች መዳረሻ በማድረግ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው
ደሴ፣ ጥቅምት16/2018 (ኢዜአ):-በአማራ ክልል ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት ለጎብኚዎች መዳረሻ በማድረግ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ደዋ ጨፋ ወረዳ የጡሩሲና መስጊድ እና ሐሪማ የመልሶ ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማት ለጎብኚዎች መዳረሻ በማድረግ የዘርፉን ገቢ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጎዱ ቅርሶችን መልሶ በመገንባት፣ በመጠገንና በማደስ የዘርፉ ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት ለምረቃ የበቃው የጡሩሲና መስጅድና ሐሪማ ግንባታም ከዚሁ ጋር የተገናኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ መሰል የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶችን የማልማትና የሀገር ሀብት ሆነው እንዲቀጥሉ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በክልሉ በሁሉም መስኮች ልማትን በማስቀጠልና ሰላምን በማፅናት ለእድገትና ማንሰራራት በጋራ መትጋት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አህመድ አሊ፣ የቱሪዝም ሀብቶችን የመጠበቅ፣ የማልማትና የገቢ ምንጭነታቸውን የማሳደግ ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጡሩሲና መስጅድና ሐሪማ በመንግስትና በህብረተሰቡ ትብብር ታሪካዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ የመልሶ ግንባታ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል።
በምረቃ ሥነ ስርአቱ ላይ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።