ቀጥታ፡

99 ጊዜ ደም በመለገስ አርአያነትን ያሳዩ የሕይወት አድን ጀግና!

የፐብሊክ ሰርቪስ ባስ ሹፌር የሆኑት አቶ ሙላት አስራት ለበጎ ተግባር ከፍ ያለ አመለካከት አላቸው። "ሰው ማገልገል ክብር ነው፤ የተቸገረን መርዳት የሕሊና እርካታ ያስገኛል" የሚለው የሕይወት መርሃቸው ነው። በዚህም መርሕ ተጉዘው በበጎ ተግባራቸው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ተስፋ ሆነዋል።

የዚህ ታሪክ መንደርደሪያ አቶ ሙላት የ99 ጊዜ የደም ልገሳ በማድረግ ላሳዩት አርአያነት በ27ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ የጤና ሚኒስቴር በልዩ ተሸላሚነት ዕውቅና የሰጣቸው መሆኑ ነው።

አቶ ሙላት ቀን ከሌት በሹፌርነት ከማገልገል በተጨማሪ፣ 99 ጊዜ ደም በመለገስ ለወገኖቻቸው በመስጠት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ችለዋል።

ይህ አስገራሚ ተግባራቸው የማይነጥፍ ደግነታቸውን ያሳያል። አዲስ አበባ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ሙላት፣ የደም ልገሳን ልማድ የጀመሩት ገና በወጣትነታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

"ገና የቀይ መስቀል ክበብ አባል ሆኜ የጀመርኩት የተቀደሰ ተግባር ዛሬም ቀጥሏል" የሚሉት አቶ ሙላት፤ ይህን የጀመሩት ደም መለገስ የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ መሆኑን በመገንዘብ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የደም ልገሳን አስፈላጊነት ተረድተው ወደ ተግባር ከተሰማሩ በኋላ ከ28 ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ በማካሄድ ታላቅ በጎነት ፈጽመዋል። 

በነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ደም የመለገስ ልምዳቸው ለጤናቸው ምንም ዓይነት እክል አለመፍጠሩን ያወሳሉ።

"ግድ የላችሁም ደም ለግሱ፤ ምንም ጤናችሁ ላይ ጉዳት አያደርስም፤ እኔም ምስክር ነኝ" ሲሉ ወጣቶችን ያበረታታሉ።

አዎ ለ99 ጊዜ ደም በመለገስ ያሳዩት ልዩ የበጎ ተግባር አገልግሎት፣ ቀኑን ጠብቆ ዕውቅና ሲሰጣቸው ስሜታቸው ልዩ ነበር። በጉባኤው ተሳታፊዎችም አቶ ሙላት ለሕይወት አድን ተግባር ባሳዩት ልዕለ-በጎነት ልዩ ቦታ ሰጥተው አመስግነዋቸዋል።

"ፈጣሪ ዕድሜና ጤና እስኪሰጠኝ ድረስ ደም መለገሴን አላቆምም" ሲሉ ለበጎ ተግባር ያላቸውን የማይለወጥ ቁርጠኝነት ያረጋገጡት አቶ ሙላት፣ በሕይወት እስካሉ ድረስ ለሰዎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል።

ወጣቶች የእርሳቸውን መልካም ተግባር በመከተል ደም እንዲለግሱም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

"የበጎነት መንፈስ የሚታየው በገንዘብ ልገሳ ብቻ ሳይሆን የራስን የሰውነት ክፍል በመስጠትም ጭምር ነው" የሚለውን አባባል ያስመሰከሩ እውነተኛ የሕይወት አድን ጀግና ናቸው አቶ ሙላት አስራት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም