ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ነው
ሳጃ፤ ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ):-ሀገር በቀል ዕውቀቶችና እሴቶችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከየም ዞን ጋር በመተባበር በየም ባህላዊ መድኃኒት እውቀት እና አጠቃቀም ዙሪያ የተዘጋጀ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በወቅቱ እንዳሉት ኢትዮጵያ በርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ ዕሴቶችና ትውፊቶች ያሏት ሀገር ናት ።
ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ እሴቶችና ትውፊቶች የህዝቦች አጠቃላይ ህይወትና የኑሮ ዘይቤ ምሶሶ መሆናቸውን አንስተዋል ።
በሀገሪቱ ያሉ ዕምቅ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ትውፊቶችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የማልማትና የማስተዋወቅ እንዲሁም ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ቀደምት አባቶች ጠብቀው ያቆዩት የየም ባህላዊ የመድሀኒት ዕውቀት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ሚኒስቴሩ እውቀቱ ለትውልድ እንዲተላለፍ በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።
በዚህ እረገድ ሌሎች ባለድርሻዎችም ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በየም ዞን ውስጥ ካሉት ዕሴቶች መካከል አንዱ የሆነው የመድሃኒት ቅመማ እውቀትን ለመጠበቅና ለማሳደግ በተቀናጀ መንገድ እየሰራን ነው ብለዋል ።
በተለይም በባህል መድኃኒት ቅመማ ረገድ ያለው እውቀት ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል ።
የየም ባህላዊ መድኃኒት ለቀማና ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን ለማሳደግና ለማዳበር ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሽመልስ እጅጉ ናቸው።
በየአመቱ ጥቅምት 17 በቦር ተራራ የሚካሄደው የመድሀኒት እጽዋት ለቀማ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር እረገድም ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል ።
እውቀቱና ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቆይና ለቀጣይ ትውልድ እንዲሸጋገር የመሰነድና ሌሎች የምርምር ስራዎችን ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በመድረኩ በዞኑ የሚገኙ የሀገር በቀል ዕውቀቶችን፣ የባህላዊ መድኃኒት እውቀትና አጠቃቀም የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ከጅማ፣ ከወልቂጤ፣ ዋቸሞና ሀረማያ ዩኒቨርስቲ ምሁራን እና ከተለያዩ አካላት ቀርቦ ወይይት ተደርጎበታል ።
በየም ባህላዊ መድኃኒት እውቀትና አጠቃቀም ዙሪያ ሲምፖዚየም እንዲሁም በባህል መድኃኒት ለቀማና ቅመማ ጋር በተያያዘ የተዘጋጀ የፎቶ ኤግዝብሽን ምልከታ ተደርጓል።
በመድረኩ የፌደራልና በየደረጃ ያሉ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።