በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የተረጂነት አስተሳሰብን ማስቀረት የሚያስችል የልማት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የተረጂነት አስተሳሰብን ማስቀረት የሚያስችል የልማት ስራ እየተከናወነ ነው
አሶሳ፤ጥቅምት 16/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የተረጂነት አስተሳሰብን ማስቀረት የሚያስችል የልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ ገለጹ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ አቡራሞ እና ሆሞሻ ወረዳዎች የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እያለማ የሚገኘውን ሰብል ጎብኝተዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት መንግሥት ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመረው ኢንሼቲቭ በክልሉ በስፋት እየተከናወነ ነው።
የክልሉ አደጋ ስጋት ኮሚሽን ኢንሼቲቩን ወደ ተግባር በመቀየር የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን በማልማት የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተያዘውን ግብ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ ለግብርና ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ራስን ከተረጂነት ማለቀቅ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባም አፈጉባዔዋ አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም እየተከናወነ የሚገኘው የግብርና ስራ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢንሼቲቩ ከተያዘለት ዓላማ በተጨማሪ የአካባቢውን የሥራ ባህል የሚቀይርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው ዓመት 1 ሺህ 756 ሄክታር ማሳ በበቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች ሰብሎች እየለማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሐመድ አብዱላዚዝ ናቸው።
ከዚህ ውስጥም ኮሚሽኑ በራሱ አቅም በአቡራሞ እና ሆሞሻ ወረዳዎች ላይ 270 ሄክታር ማሳ እያለማ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተጀመረው እንቅስቃሴ የተለያዩ ወረዳዎች ወደ ስራ መግባታቸውንና ይህም ለኮሚሽኑ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።