የአካባቢያችንን ሠላምና አንድነት አጠናክረን ለማስቀጠል ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም እንሰራለን-የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ሠላምና አንድነት አጠናክረን ለማስቀጠል ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም እንሰራለን-የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች
ወልዲያ፤ ጥቅምት 16/2018(ኢዜአ):- የአካባቢያቸውን ሠላምና አንድነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም እንደሚሰሩ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
118ኛው የመከላከያ ሠራዊት የምስረታ ቀን በዓል ዛሬ በወልዲያ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ ከተገኙት ነዋሪዎች መካከል አቶ አበባው ወደደኝ እንደገለጹት፣ ሠራዊቱ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ለሀገር ዳር-ድንበር መከበር መስዋዕትነት የሚከፍል መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው ታጥቆ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ጽንፈኛ ቡድን አደብ በማስገዛት የአካባቢያቸው ሰላምና ደህንነት ማስጠበቁን ገልጸው፣ ሰላሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ከሠራዊቱ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።
የወልዲያ ከተማና አካባቢው ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ በተለያየ መንገድ ሲያደርጉት የነበረው እገዛ ማጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል።
"ህዝቡ ለሠራዊቱ የተለመደ ደጀንነቱን ዛሬም አጠናክሮ ቀጥሏል" ያሉት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊና የከተማው ነዋሪ አቶ ቢሆነኝ ካሣው ናቸው።
የህዝብን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ውድ ህይወቱን ጭምር እየከፈለ ላለውና የአገር ዘብ ለሆነው መከላከያ ሠራዊታችን የምናደርገው ድጋፍና የምንሰጠው ፍቅር በቀጣይም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የዛሬው በዓልም ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡትን በቁርጠኝነት በመታገል የአካባቢያችንን ሠላም ለማስጠበቅ ዳግም ቃል የምንገባበት መሆን አለበት ብለዋል።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ኢትዮጲስ አያሌው የቀደሙ አባቶቻችን ያቆዩልንን የፍቅርና የአንድነት እሴት የአሁኑ ትውልድም አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
ይህ እሴት ተጠናክሮ በከተማው የልማት እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ህብረተሰቡ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም ሌት ተቀን እየተጋ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት በመደገፍ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ11ኛ ዕዝ የሠራዊት ሥነ ልቦና ግንባታ ኃላፊ ኮሎኔል አክሊሉ አበበ በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊት ዋና ተግባሩ የሀገርና የህዝብ ሠላምን ማስጠበቅ መሆኑን አንሰተዋል።
"ሠራዊቱን የሚያስጨንቀው የህዝብ ሠላም ሲታወክና የአገር ሉኣላዊነት ሲደፈር ነው፤ ለዚህም ሠራዊታችን ውድ ህይወቱን ጭምር እየከፈለ የህዝብ ሠላምና የሀገርን ዳር ድንበር ጭምር ያስከብራል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሠራዊቱ የባዳዎችን አጀንዳ ለማስፈጸም እየተላላኩ ያሉ የጥፋት ቡድኖችን እያሳደደና እየደመሰሰሰ ይገኛል ብለዋል።