የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ለገበያ መረጋጋት ሚናቸውን እየተወጡ ነው-ሸማቾችና ነጋዴዎች - ኢዜአ አማርኛ
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ለገበያ መረጋጋት ሚናቸውን እየተወጡ ነው-ሸማቾችና ነጋዴዎች
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፡-በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የተለያዩ የምርት ዓይነቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ለገበያ መረጋጋት ሚናቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።
መንግሥት በቅዳሜና እሁድ ገበያዎችና ተግባራዊ ባደረጋቸው የተለያዩ ኢኒሼቲቮች የምርት አቅርቦትን በማሳደግ፣የዋጋ ንረትን በመቆጣጠርና ገበያን በማረጋጋት እንዲሁም የኑሮ ጫናን በማቃለል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ዋነኛ ዓላማም ሸማቾች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻል ሲሆን፤ ገበያዎቹ ምርቶቹን ከአርሶ አደሮች፣ ከፋብሪካዎች ወይም ከሸማቾች የኅብረት ሥራ ማህበራት በቀጥታ በመረከብ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ኢዜአ በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሸማቾችና ነጋዴዎች በገበያዎቹ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በእሁድ ገበያ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ሽታ ደመላሽ የሚፈልጉትን ምርት በበቂና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአካባቢያቸው መከፈታቸው ለግብይት የሚያስፈልገውን ጊዜና የትራንስፖርት ወጪ እንደቆጠበላቸው ገልጸዋል።
ሌላኛው ሸማች አባቡ አሰፌ በበኩላቸው፤ የገበያዎቹ በቅርብ ርቀት ተደራሽ መሆን ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የፈለጉትም ምርት እንዲያገኙ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ገበያዎቹን የበለጠ በማስፋፋት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
አቶ መለሰ ባዬ በበኩላቸው፥የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በእሁድ ገበያ ላይ በመሳተፍ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ ከኅብረት ሥራ ማህበራት እና ከአቅራቢዎች በቂ ምርት እያመጡ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ከነጋዴዎቹ መካከል ምትኩ ፋንታሁን እንደሚሉት፤ መንግሥት የንግድ ቦታዎችን በነጻ ከማመቻቸቱ ባሻገር ምርቶችን ከአቅራቢዎች በቀላሉ በማግኘት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ አስችሏቸዋል።
ይህም ምርቶችን በበቂ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብ ጥሩ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
ሌላኛዋ ነጋዴ ገነት ዋቅጅራ፤ ለሸማቾች በርካታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሳ ፤ ኅብረተሰቡ በመገበያያ ቦታዎቹ በመገኘት የሚፈልገውን ምርት እየገዛ መሆኑን ተናግራለች።