እምቦጭን በዘላቂነት ለመከላከል የህብረተሰብ ተኮር ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
እምቦጭን በዘላቂነት ለመከላከል የህብረተሰብ ተኮር ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፡-እምቦጭን በዘላቂነት ለመከላከል የህብረተሰብ ተኮር ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ ሞቱማ መቃሳ ገለጹ፡፡
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ ሞቱማ መቃሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ለማከናወን የውኃ ሀብቷን መጠበቅ ወሳኝ ነው።
ስለሆነም መንግስት በአገሪቷ የልማት እቅዶች ውስጥ የውኃ አስተዳደርና ጥበቃን ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለአብነትም በአገሪቷ ውስጥ ምን ያህል የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃ ሀብት እንዳለ በትክክል የመለየትና የመመዝገብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህን ሀብት ለየትኞቹ የልማት ዘርፎች በምን ያህል መጠንና ጥራት ለማዋል እንደሚቻል የውኃ አቅም ልየታ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የውኃ ሀብት አስተዳደርና ጥበቃ ስራ ከፍ ብሎ እንዲመራ ሚኒስቴሩ መዋቅራዊ ማሻሻያ ማድረጉንም አመልክተዋል።
ከፍተኛ ትኩረት ከሚሹ የውኃ አካላት ጥበቃ ጉዳዮች መካከል አንዱ በእምቦጭ አረም ምክንያት የሚከሰተውን ችግር ማቃላል መሆኑን አመልክተዋል።
እምቦጭ በፍጥነት የሚስፋፋና በየጊዜው ተመልሶ የሚመጣ መሆኑን ያወሱት አቶ ሞቱማ፤ በዘላቂነት ለማቃለል በየጊዜው አስቸጋሪ ፈተና መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን ችግር መፍትሄ ለመስጠት ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራበት እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ይህን ዘላቂ ችግር ለማቃለል ህብረተሰብን ያማከለ አሰራር ተቀይሶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝና ውጤትም እየተገኘበት እንደሆነም አስታውቀዋል።
በጣና ሐይቅና በሌሎች የውኃ አካላት ላይ የእምቦጭ አረምን ችግር ለመፍታት ከተጀመሩ ሥራዎች በተጨማሪ ህብረተሰብ ተኮር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ሞቱማ ተናግረዋል።
የውኃ ሀብት ጥበቃና አስተዳደር የሀገር ጉዳይ በመሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና መላው ህብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።