ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋን ማደግና የፓርኮች ልማት አዕዋፍትንና የዱር እንስሳትን ከስደት ታድጓል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፡-በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከናወነው ሥራ የደን ሽፋን ማደግና የፓርኮች ልማት አዕዋፍትንና የዱር እንስሳትን ከስደት እየታደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 16ኛውን ዓለም አቀፍ የስደተኛ አዕዋፍ ቀንን "ለአዕዋፍት የተመቸ ማህበረሰብ እና ከተማ እንፍጠር" በሚል መሪ ሃሳብ በአቢጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ አክብሯል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ቀኑን ማክበር ያስፈለገው ለህብረተሰቡ ስለ እንስሳት ሀብት ጥበቃ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።

አዕዋፋትና የዱር እንስሳት በመኖሪያ አካባቢያቸው በሚደርስ መራቆት ምክንያት ለስደት እንደሚዳረጉ ተናግረው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን ገልጸዋል።

የአዕዋፍት እና የዱር እንስሳት ስደት ችግርን ከስር መሰረቱ ለመፍታት የጥበቃ ቦታዎችን ማልማትና ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገር ደረጃ የደን ሽፋን ማደጉን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ለዱር እንስሳት ምግብና መጠለያ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አብራርተዋል።

የአካባቢ ጥበቃ እያደገ በመምጣቱ ሐይቆችም ወደ ድሮ ይዞታቸው መመለሳቸውን አመላክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ፓርኮችን የመጠበቅ እና አዳዲስ የጥበቃ ስፍራዎችን የማልማት ተግባራት በስፋት ማከናወናቸውን ጠቁመዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የአዕዋፋት እና የዱር እንስሳት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክተው፤ የፓርኮችን ይዞታ በማሻሻልና ያሉትን በመጠበቅ ተሰደው የቆዩ የዱር እንስሳት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ማስቻሉንም አስታውቀዋል።

የዱር እንስሳት ለአደጋ ተጋላጭነት በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን አንስተዋል።

በመርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር፣ ባለድርሻ አካላት፣ አርቲስቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና የባለስልጣኑ ሰራተኞች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም