ቀጥታ፡

በዓሉ ህዝቦች ባህላቸውን በአደባባይ እንዲገልጹና እንዲያስተዋውቁ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው-- የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዳማ፤ ጥቅምት 16/2018(ኢዜአ)፡-የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ህዝቦች ባህላቸውን በአደባባይ አውጥተው እንዲያስተዋውቁ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።

ዘንድሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በማስመልከት የተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ያተኮረና ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው ።


 

በመድረኩ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ እንደገለፁት በዓሉን በየዓመቱ ከማክበር ባለፈ በፌዴራሊዝምና ህገ መንግስት አስተምህሮ ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም ዜጎች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖራቸው እንዲሁም የህዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክም በዓሉን በማስመልከት የፌዴራሊዝምና ህገ መንግሥት አስተምህሮን ይበልጥ ለማስረፅ በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ ግልጽነትና ለመፍጠርና በቀጣይ በየደረጃው የሚከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ለማሳካት ያለመ ነው ብለዋል።

በዚህም በፌዴራልና በክልል ደረጃ ባሉ ተቋማት እንዲሁም በዞኖች፣ በወረዳዎችና ከተሞች ላይ በፌዴራሊዝምና ህገመንግስት አስተምህሮ ላይ ለህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ ማስረጽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የተሳካ ለማድረግም ከፌዴራል ጀምሮ በክልል፣ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች በተከታታይ እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።

በዓሉ የባህል ልውውጥና ትውውቅ እንዲሁም የህዝቦች ግንኙነትና ትስስር የሚጠናከርበት ከመሆኑ ባለፈ ባህሎቻቸውን በአደባባይ የሚያሳዩበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፌዴራሊዝምና ህገ መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል ዳይሬክተር ሃይለኢየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ናቸው።

በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ ፌዴራሊዝም የህዝቦች ውክልና በተግባር የሚገለፅበት ነው ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የፌዴራል ስርዓቱን ከማጠናከር አንፃር በርካታ አካታችና ሚዛናዊ የሆኑ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ የህዝቦች ባህል፣ ማንነትና ትስስር ይበልጥ ጎልቶ የሚወጣበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓሉ "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበር ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም