በድሬዳዋ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 16/2018(ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።
በአስተዳደሩ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ያስገነቧቸው 80 ቤቶች ዛሬ ተመርቀው ለችግረኛ ቤተሰቦች ተሰጥተዋል።
ቤቶቹን መርቀው ለችግረኞችና ለአረጋዊያን ቁልፉን ያስረከቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን፣ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ምክር ቤት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በበጎ ፍቃድ ሥራዎች እርስ በርስ ለመደጋገፍ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኙ ናቸው።
በተለይም የማህበረሰቡን ችግሮች በማቃለል እና ተጨባጭ መፍትሄ በማምጣት የጎላ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።
ዛሬ ተመርቀው ለችግረኞች የተላለፉት ቤቶች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው ይሄ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ በበጋ ወራትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በቅንጅት የሚሰራው ሥራ የሚበረታታና በሌሎቹም የልማት መስኮች ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሳተፉ ተቋማት በአጭር ጊዜ መኖሪያ ቤቶችን በጥራት ገንብተው ለችግረኞች በማስተላለፋቸው አመስግነው ይሄ የመደጋገፍ ባህል ይበልጥ ማስፋትና ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
"በበጎ ፍቃድ ሥራ በመሳተፍ የዜጎችን ችግሮች መፍታት ደስታና እርካታ ያጎናፅፋል" ያሉት ደግሞ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስተባባሪው የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ናቸው።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ300 ሺህ በላይ የአስተዳደሩ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ 14 ዓይነት የበጎ ፍቃድ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በልማት ስራው ከ90 ሺህ በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን አስታውሰው ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ በዚሁ መርሃግብር የተገነቡ ሌሎች ቤቶች ተመርቀው ይተላለፋሉ ብለዋል።
ዛሬ የቤት ባለቤት የሆኑት አረጋዊያን በበኩላቸው የተመረቁትን ቤቶች የዘመናት ጥያቄያቸውን የሚፈቱና የተሻለ ህይወት ለመኖር የሚያስችሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአስተዳደሩ በ14 ሚሊዮን ብር የተገነባው ዳዊት ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከልም ተመርቋል።