ቀጥታ፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከሐረሪ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር ለአቅመ ደካሞች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ

ሐረር፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ) ፡-የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከሐረሪ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር በክልሉ ለአቅመ ደካሞች ያስገነባውን የመኖሪያ ቤት አጠናቆ አስረከበ።

በክልሉ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ ስምንት መኖሪያ ቤቶች የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በተገኙበት ዛሬ ርክክብ ተካሂዷል።


 

በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ በለውጡ ዓመታት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያጎለብት በርካታ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።


 

በተለይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ የአቅመ ደካሞችና ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ችግር በማቃለል ረገድ አበረታች ለውጥ ተገኝቶበታል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን ከማሳደግ ባለፈ ዜጎች ንጹህ መኖሪያ ቤትና ለኑሮ ምቹ አካባቢ እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል።


 

በዚህም ሚኒስቴሩ የበኩሉን ለመወጣት 20 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን በመገንባትና አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት ማስረከቡን ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በወቅቱ እንዳሉት የክልሉ መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፋፊ ሥራዎችን አከናውኗል።


 

በተለይ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ዜጎችን የመደገፍና የማገዝ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።


 

ዛሬ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተላለፉት ስምንት መኖሪያ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራትና በፍጥነት ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎቹ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ከፌዴራል የመጡ ባለስልጣናትና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ነዋሪዎችና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም