ቀጥታ፡

አስተዳደሩ ቤት ለመስራት የቆጠቡ መምህራን ወደ ግንባታ ሂደት እንዲገቡ ቦታ እያስረከበ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018(ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤት ለመስራት 25 በመቶ ገንዘብ የቆጠቡ መምህራን ወደ ግንባታ ሂደት እንዲገቡ ቦታ እያስረከበና ሌሎች ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመምህራንን የቤት ችግር ለመፍታት 25 በመቶ ሲቆጥቡ ቀሪውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር እንዲያቀርብላቸው የሚያስችል ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

መምህራን ከሚያነሷቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መካከል የቤት ጉዳይ መሆኑን ያወሱት የቢሮ ኃላፊው፤ ከተማ አስተዳደሩ ለመምህራን ተገቢ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመምህራንን የቤት ግንባታ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀመጠውን የ25 በመቶ ቁጠባና 75 በመቶ ብድር ለሚያሟሉ መምህራን እና ለተደራጁ ማህበራት የቤት ግንባታ ለማስጀመር ሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ስድስት ሺህ መምህራን ተመዝግበው ቅድመ ክፍያውን በማጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚቀርበውን 75 በመቶ ብድር ለማስጀመር ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

ከዚህም በሚቀጥሉት 15 ቀናት ወደ ግንባታ ሂደት ለመግባት ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የቦታ ማስረከብና የኮንትራት መረጣ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ቤት ቅድሚያ ለመምህራን ለመስጠት በገባው ቃል መሰረት የብድር አገልግሎት ማመቻቸቱንና መሬት በነጻ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

መምህራን ከተማ አስተዳደሩ ያመቻቸውን ዕድል ለመጠቀም ፈጥነው 25 በመቶውን በመቆጠብ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም