ቀጥታ፡

በበጎ ፈቃደኞች ቤታችን በአዲስ መልክ መሰራቱ ችግራችንን ፈቶልናል

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፡-ቤታችን በበጎ ፈቃደኞች በአዲስ መልክ መሰራቱ የዘመናት ችግራችንን ፈቶልናል ሲሉ  በሀዋሳ ከተማ ቤታቸው የታደሰላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ በበኩሉ በወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ690 በላይ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ግንባታና እድሳት ሥራ መከናወኑን አስታውቋል።

በክረምቱ ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ ዘርፎች ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በሀዋሳ ከተማ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች እድሳትና አዲስ ግንባታ ሥራ አንዱ ሲሆን በዚህም ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። 

በከተማዋ ቤታቸው ታድሶላቸው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በምስራቅ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት አቶ ዶሰኛው ወልደጊዮርጊስ ደጋፊ  የሌላቸው በመሆኑ በደሳሳ ጎጇቸው ለጸሐይና ዝናብ ተጋልጠው ለብቻቸው ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአካባቢው ወጣቶች ቤታቸውን በአዲስ መልክ እንደገነቡላቸው ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም የማዕድ ማጋራትና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

የተደረገልኝ ድጋፍ ጠያቂና ደጋፊ ወገን እንዳለኝ ያክል ተሰምቶኛል ያሉት ነዋሪዋ፣ በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ወይዘሮ እጅጋየሁ ታደሰ የተባሉ ሌላው ነዋሪም በበፊቱ ጎጇቸው ለዝናብ፣ ለጸሐይና ለመጥፎ ሽታ ተጋልጠው በችግር ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ቤታቸው በብሎኬት በአዲስ መልክ ተሰርቶ መረከባቸውን ተናግረዋል።

"ከሰው እኩል በደስታ መኖር ጀምሬያለሁ" ያሉት ወይዘሮ እጅጋየሁ "የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የነበረብንን ችግር ከመፍታት ባለፈ የዘመናት ከሰው እኩል አድርጎናል" ብለዋል

በጤና እክል ምክንያት ታመው የአልጋ ቁራኛ እንደነበሩና መኖሪያ ቤታቸው ዘሞ ሊወድቅ የደረሰ እንደነበር የሚገልጹት ደግሞ ወይዘሮ ወርቂቱ አያኖ ናቸው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሀዋሳ ከተማ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ወልደፃዲቅ በበኩላቸው በከተማዋ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉና ባህል እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፈው ክረምት ከ690 በላይ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች እድሳትና አዲስ ግንባታ መከናወኑን ገልፀው፣ ከነዚህ ውስጥ 230 ቤቶች ፈርሰው በአዲስ የተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳትና አዲስ ግንባታ በተጨማሪ በደም ልገሳ፣ በማዕድ ማጋራት፣ ቀጣይነት ባለው የምገባ መርሃ ግብር፣ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች አገልግሎቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ መከናወኑንም አመልክተዋል፡፡

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ316 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን 201 ሚሊዮን የሚጠጋ ወጪንም ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

ሌሎች ስራዎችም እንዲሁ በንቅናቄ መከናወናቸውን ያወሱት ኃላፊዋ በበጋ ወቅትም ይህ ሥራ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከናወን ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም