በኢትዮጵያ የፉክክርና የምክክር ሚዛኑን የጠበቀ ጤናማና የዳበረ የፖለቲካ ምህዳር የመገንባት ሥራ እየተከናወነ ነው-አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የፉክክርና የምክክር ሚዛኑን የጠበቀ ጤናማና የዳበረ የፖለቲካ ምህዳር የመገንባት ሥራ እየተከናወነ ነው-አቶ አደም ፋራህ
ባህር ዳር፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የፉክክርና የምክክር ሚዛኑን የጠበቀ ጤናማና የዳበረ የፖለቲካ ምህዳር የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።
የአማራ ክልል መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፣የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ እንደገለጹት፥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ በምክክርና በፉክክር ላይ መሰረት ያደረገ የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት እየተገነባ ይገኛል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ጠንካራ ህገ መንግስት እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች የህግ ማዕቀፎች፣ተቋማዊ አደረጃጀቶችና ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልፀዋል።
እንዲሁም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ አማራጭ ሀሳባቸውን በነፃነት ለህዝብ የሚያደርሱበት ምህዳር መመቻቸቱንም አክለዋል።
በተጨማሪም እርስ በእርሳቸው የሚመካከሩበት የሚወያዩበትና የሚነጋገሩበት እንዲሁም ገዥውን ፓርቲ የሚሞግቱበት አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ፓርቲዎች ህግና ስርዓት አክብረው የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር እና ለሰላምና መረጋጋት መስፈን መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል ፅንፈኛ ቡድኖች በህዝብ ላይ እያደረሱ ያለውን በደል ለማስቆምም ፓርቲዎች በትብብር በመስራት ለዳበረ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፥ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በሀገራችን የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህ ለዳበረ የፖለቲካ ልምምድ ሰላማዊ አማራጭን በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አዎንታዊ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በኋላ ቀር አካሄድ የፖለቲካ ስልጣንን በሀይል ለመያዝ ፋላጎቱ ያላቸው ፅንፈኛ ቡድኖች በክልሉ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ የሚስተዋለውን ችግር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሰለጠነ አግባብ በመነጋገር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፥ የጋራ ምክር ቤቱ የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት በኩል ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
በዚህም ፓርቲዎች በመመካከርና በመነጋገር የሚገጥሙ ችግሮችን በሰለጠነ አግባብ በትብብር መፍታት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ይህም በሀገሪቱ በምክክርና በፉክክር የተመሰረተ ጤናማ የዳበረ የፖለቲካ ምህዳር እንዲገነባ የጋራ ምክር ቤቱ እየሰራ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ በጋራ ለጋራ ህዝባችን የምንወያይበት መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል።
በመድረኩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛል።