ቀጥታ፡

ውብ ሐረርን ለትውልድ ለማሻገር …

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፡- ሰሞኑን በሳንፍራንሲስኮ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ሐረር ከተማን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ለማድረግ የተጀመረው ኢንሼቲቭ እያስገኘ ላለው ውጤት ዕውቅና ተሰጥቷል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሐረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለአሁኑ ነዋሪ ብሎም ለመጪው ትውልድ ጽዱ፣ ውብ እና ምቹ ሐረርን ለማንበር ያለሙ ስምምነቶች ተፈርመው እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ከእነዚህ ስምምነቶች አንዱ ‘ኪዩቢክ ፕላስቲክ ፕራይቬት’ የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት እና የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2024 የተፈራረሙት አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ የውል ስምምነት መሠረትም፤ ቤት ለቤት እና ከድርጅቶች የሚሰበሰቡ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ደረቅ ቆሻሻዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ ከሚሰበሰበው ቆሻሻ እስከ 48 በመቶ ያህሉ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ቆሻሻ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ቆሻሻ በንፋስ ምክንያት እየተበተነ አካባቢን እንደሚበክል አስገንዝበው፤ ይህን ከማስቀረት አልፎ ከየቤቱና ድርጅቶች የሚወጣው የፕላስቲክ ቆሻሻ ተለይቶ ‘ፕሮሰስ’ ተደርጎ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ስምምነቱ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህም መሠረት ከፕላስቲኩ በሚሠራ ጡብ የቤት ግንባታ እንደሚከናወን ተናግረዋል። ለአብነትም ከ500 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ፕላስቲክና ፕላስቲክ ነክ ቆሻሻ ወደ ፕሮሰስ በማስገባት፤ በሐረር ከተማ ጁገል አካባቢ ቤተ መጻሕፍት መገንባቱን አረጋግጠዋል።

ከዚህ በመነሳት ወጪ ቆጣቢ ስለሆነ ለሌሎች ቤቶች ግንባታ እንደሚውልም በጥናት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

የሚሰበሰበው የፕላስቲክ ቆሻሻ በበዛ ቁጥር እንደገና የሚሰጠው ጥቅምም በዚያው ልክ ያድጋል ብለዋል።

ሕብረተሰቡን የማስተማር ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ በተለይ ሴቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር በሚሰበስቡት ፕላስቲክ ልክ ገንዘብ እየተከፈላቸውም መሆኑን ነው የገለጹት።

እስካሁንም ከ600 በላይ ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

ቆሻሻን በአግባቡ በመሰብሰብ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ ባለው ጥረት በሐረር ከተማ በየአካባቢው ይታይ የነበረው የፕላስቲክነክ ደረቅ ቆሻሻ መቀነሱን አረጋግጠዋል።

አሁን እየተገኘ ያለው ውጤት በቀጣይ ብዙ ለመሥራት ዐቅም እንደሚሆንም አመላክተዋል።

ለዚህ ጥሩ ጅማሮም ሐረርን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት ነጻ ለማድረግና ፕላስቲክ ቆሻሻን እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል እየተደረገ ላለው ጥረት በሳንፍራሲስኮ የተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ዕውቅና ሰጥቶናል ብለዋል።

ከዕውቅናው በፊት የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በሐረር ተገኝተው ግምገማ ማድረጋቸውንም አውስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህም በአንድ ወቅት መጥተው መጎብኘታቸውን እና ወደ ሌሎች ከተሞችም መስፋት ያለበት ጥሩ ተሞክሮ መሆኑን መግለጻቸውን ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡም ፕላስቲክን ከሌሎች ቆሻሻዎች ጋር ቀላቅሎ ከመጣል ተቆጥቦ በአግባቡ እንዲወገድ የማድረግ ልምዱ እየዳበረ መሆኑን አንስተው፤ለነዋሪ ምቹና ጽዱ ሐረርን ለማንበር በሚደረገው ጥረት የሕብረተሰቡ ሚና እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም