ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የሚያስቆጭ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የሚያስቆጭ ነው
አዶላ፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የሚያስቆጭ መሆኑን መምህራን ገለጹ፡፡
ለዘመናት የራሷ የባህር በር የነበራት ኢትዮጵያ ከባህር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ቢሆንም ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ የባህር በሯን አጥታ የተቆለፈባት ሀገር ሆናለች።
የኢትዮጵያ መንግስት የባህር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ መሆኑን በጽኑ በማመንና ጠንካራ አቋም በመያዝ በዲፕሎማሲው ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑም የሚታወቅ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዶላ መምህራን ኮሌጅ መምህራን፥ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ያጣችበት መንገድ የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተዋል።
ለዘመናት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ የሆነውን የባህር በር ለማግኘት ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ ነው መምህራኑ የሚገልጹት።
የኮሌጁ የሰው ሀብት አቅም ግንባታ አስተዳደር ዲን ክብረወርቅ አለማየሁ፥ የባሀር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ እንጂ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያዊያን ተባብረን እንደጨረስነው ሁሉ የባህር በርን ለማግኘት መንግስት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚያደርገውን ጥረት ሁሉም ዜጋ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስት በድርድር፣በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ እየሄደበት ያለው ርቀት የሚያስመሰግነው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የአንድ ሀገር ሰላምና ልማት ለሁሉም ጎሮቤት ሀገራት የሚተርፍ በመሆኑ ሌሎች ሀገራት የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎትና መሰረታዊ ጥያቄዎች ሊቀበሉ ይገባል ብለዋል።
በኮሌጁ የእቅድና ትምህርት አስተዳደር መምህር ወንድሙ አስፋው፥ ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን እውን ለማድረግ በምታደርገው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩት ዜጎቿ ሁሉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምጽ ማሰማት አለባቸው ብለዋል፡፡
የባህር በር ማግኘት ለሰላም፣ልማትና እድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በዲፕሎማሲ ጫና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማሳመን የባህር በር እንድታገኝ ሁላችንም ለሀገራችን ድምጽና አምባሳደር መሆን አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በኮሌጁ የትምህርትና ዕቅድ አስተዳደር መምህር ሌሊሳ ኤቢሳ በበኩላቸው፥ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተጀመረው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ በባህር በር ይደገማል ብለዋል፡፡
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የባህር በር ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ቀላል የማይባል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ማስተናገዷን አንስተዋል።
የባህር በር ጥያቄውን በድርድርና በውይይት ለመፍታት መንግስት የጀመራቸው ተግባራት እውን እንዲሆኑም የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በህዝብ ተሳትፎ እውን እንደሆነው ሁሉ ትውልዱ የባህር በር ለማግኘትም የተባበረ ክንዱን በማሳየት ሌላ ታሪክ እንደሚሰራም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡