261ኛው የኤል ክላሲኮ ደርቢ - ኢዜአ አማርኛ
261ኛው የኤል ክላሲኮ ደርቢ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ):- በስፔን ላሊጋ የ10ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ15 ላይ 84 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሳንቲያጎ በርናባው ስታዲየም ይካሄዳል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ሪያል ማድሪድ በ24 ነጥብ አንደኛ፣ ባርሴሎና በ22 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።ሪያል ማድሪድ በላሊጋው እስከ አሁን ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች በስምንቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
በጨዋታዎቹ 20 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ጎሎችን አስተናግዷል።ባርሴሎና ከዘጠኝ የላሊጋ ጨዋታዎች ሰባት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 24 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦች ተቆጥረውበታል።
የሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው። ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ1902 ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ባርሴሎና 3 ለ 1 አሸንፏል።
ቡድኖቹ በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 260 ጊዜ ተገናኝተዋል።
ሪያል ማድሪድ 105 ጊዜ ድል ቀንቶታል። ባርሴሎና 103 ጊዜ ሲያሸንፍ 52 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።በጨዋታዎቹ ሪያል ማድሪድ 437፣ ባርሴሎና 431 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በላሊጋው 190 ጊዜ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ 79 ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና 76 ጊዜ አሸንፏል። 35 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
በዣቪ አሎንሶ የሚመራው ሪያል ማድሪድ የመልሶ ማጥቃት የአጨዋወት ስልት፣ የግብ እድሎችን በሚገባ መጠቀም እና የተከላካይ መስመር ጥንካሬው የዘንድሮው የውድድር ዓመት መገለጫዎች ናቸው።
ቡድኑ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወቅት የተከላካይ ክፍሉ ለአደጋ ተጋላጭ መሆኑ እንደ ድክመት ይነሳል።
የሃንሲ ፍሊኩ ባርሴሎና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ፣ የመሐል ሜዳ የጨዋታ ፍሰት፣ የተጫዋቾች የቦታ አያያዝ እና ወጣት ተጫዋቾች ክህሎት መጠቀም ጥንካሬዎቹ ተደርገው ይነሳሉ።
በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ የተከላካይ ክፍል መስመሩ ለአደጋ መጋለጥ የቡድኑ ዋንኛ ክፍተት ነው።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጠንካራ ስሜት እና ግለት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የ45 ዓመቱ ሴዛር ሶቶ ግራዶ ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።