ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ ከቀኑ 11 ሰዓት በኤምሬትስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።

የሰሜን ለንደኑ አርሰናል በ19 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ክሪስታል ፓላስ በ13 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። 

አርሰናል በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ስድስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 

መድፈኞቹ በጨዋታዎቹ 15 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሶስት ግቦችን አስተናግደዋል።

የደቡብ ለንደኑ ክሪስታል ፓላስ በበኩሉ ከስምንት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሽንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። 12 ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዷል። 

የለንደን ክለቦቹ በፕሪሚየር ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ33ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በነበሩ 32 ጨዋታዎች አርሰናል 21 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። 

ፓላስ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አምስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። 

አርሰናል በጨዋታዎቹ 70 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ክሪስታል ፓላስ 33 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት እ.አ.አ አፕሪል 2025 ሲሆን ኤምሬትስ ስታዲየም ላይ በተካሄደው ጨዋታ ቡድኖቹ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

የዛሬው መርሃ ግብር አርሰናል የሊጉን መሪነት ለማጠናከር፣ ፓላስ በጥንካሬው ለመቀጥል የሚያደርጉት መሆኑ ተጠባቂ ያደርጋል። ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የ35 ዓመቱ ቶም ብራሞል ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል። 

በሌሎች ጨዋታዎች አስቶንቪላ በሊጉ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማንችስተር ሲቲን ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ያስተናግዳል።

ዎልቭስ ከበርንሌይ እና ቦርንማውዝ ከኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በኤቨርተን እና ቶተንሃም ሆትስፐርስ መካከል ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም