ኢትዮጵያ መድን ከወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ፒራሚድስ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ መድን ከወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ፒራሚድስ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከግብጹ ፒራሚድስ ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት ላይ በካይሮ በሚገኘው ጁን 30 ስታዲየም ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው ዙር የዛንዚባሩን ምላንዴጌን በድምር ውጤት 4 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።
ተጋጣሚው ፒራሚድስ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የሩዋንዳውን ኪዮቩ ስፖርትስ በድምር ውጤት 5 ለ 0 በመርታት ሁለተኛውን ዙር ተቀላቅሏል።
ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲሳተፍ የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው።
ቡድኑ አምናው በታሪኩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ለመጀመሪያ ጊዜ በማሸነፍ በአህጉራዊ ውድድሩ የሚያሳትፈውን እድል እንዲያገኝ አስችሎታል።
የግብጹ ፒራሚድስ ክለብ የወቅቱ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ባለቤት ነው።
ፒራሚድስ እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዓመት ለፍጻሜ የደቡብ አፍሪካውን ማሜሎዲ ሳንዳውንስ በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል። በቅርቡ የሞሮኮውን ቤርካኔ በካፍ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በመርታት ዋንጫ አንስቷል።
የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ መድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድልን ይቀላቀላል።