የነዳጅ ኩባንያዎች አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያተኮረ አዲስ የገበያ ድርሻ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ኩባንያዎች አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያተኮረ አዲስ የገበያ ድርሻ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው
 
           አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):-የነዳጅ ኩባንያዎች አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያተኮረ አዲስ የገበያ ድርሻ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ የነዳጅ ኩባንያዎች የነዳጅ ስርጭት ፍትሃዊነትና ተደራሸነትን ማሻሻል የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ትግበራን አስመልክቶ ውይይት አካሄዷል።
                
                
  
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለነዳጅ ስርጭት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት አዲስ የአሰራር ለውጥ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።
በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ ያለው የነዳጅ ስርጭት አሰራር የነዳጅ ኩባንያዎች የገበያ ድርሻን በሁሉም አካባቢዎች የማድረስ አቅም መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኩባንያዎች አብዛኛውን የነዳጅ መጠን ለራሳቸው ማደያዎች የማሰራጨት፣ በሁሉም አካባቢዎች ተቀራራቢ የነዳጅ ስርጭት ባለመኖሩ እንዲሁም የነዳጅ አቅርቦት ቅሬታዎች መኖራቸውን በጥናት መለየቱን አንስተዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት የኩባንያዎች አዲስ የገበያ ድርሻ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በዚህም በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ማደያዎችን ነዳጅ ፍጆታ መነሻ ያደረገ በኢኮኖሚ አቅማቸውና የነዳጅ ተጠቃሚዎች መጠን፣ የኢኮኖሚ ኮሪደር ከተሞች መሰረት በሰባት ክላስተሮች መመደባቸውን ገልጸዋል።
የነዳጅ አቅርቦት ቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው የመንግስት የልማት ዘርፎች፣ ፕሮጀክቶችና ኢንዱስትሪዎች የነዳጅ ተደራሽነት እንዲሻሻል እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
ከጅቡቲ ጀምሮ የነዳጅ ስርጭቱን በጂፒ ኤስ ለመከታተል የሚያስችል አሰራርም ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ይህም የነዳጅ ስርጭቱን ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ላይ ጉልህ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎችን ተወካዮች በሰጡት አስተያየት ከህገ ወጥ የነዳጅ ስርጭት ክትትልና ቁጥጥር፣ ከነዳጅ ማደያዎች አቅም፣ ከነዳጅ አቅርቦት ፍላጎት፣ ከጭነት ፕሮግራም፣ ከቴክኖሎጂ አቅርቦት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አንስተዋል።
                
                
  
በዘርፉ የሚያጋጥመውን ብልሹ አሰራር ለመከላከልም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
                
                
  
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) ባለስልጣኑ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ ኦን ላይን መሰጠት የሚችሉ አገልግሎቶችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የነዳጅ ማደያዎችን አቅም ለማጠናከር፣ ደረጃቸውን የጠበቁና ወጥ ለማድረግ የነዳጅ ኩባንያዎች የአቅም ግንባታ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ህገ ወጥ አሰራሮችን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።