በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ትስስር ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ትስስር ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):-በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
11ኛው ጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ሲሆን መሪዎች፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ልዩ መልዕክተኞች ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በፎረሙ ላይ አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ በሰላምና ደህንነት፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች የሚገጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት፤የአፍሪካ ሀገራት በራስ አቅም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ይገባል።
ወጣቶች እና ሴቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ መበልጸግ አቀጣጣይ ሞተር እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ትኩረት ይፈልጋሉ ብለዋል።
ከኢንቨስትመንት አኳያም በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎች እና ቢዝነስ ተቋማት ኢንቨስት አድረገው አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲፋጠን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢንቨስት በማድረግ የሥራ ዕድል በመፍጠር ቀጣናዊ ትስስር እንዲጠናከር አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
የኬኒያ ቴሌኮም ኦፕሬተሮችም በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እና ናይጄሪያዊው ባለኃብት አሊኮ ዳንጎቴም በኢትዮጵያ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት መጀመሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ ውስጥ የሚደረጉ መሰል የኢኮኖሚ ትስስሮች ለአፍሪካ ብልጽግናና ሉዓላዊነት መረጋገጥ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የቀድሞ የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ጆአኪም ቺሳኖ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ አገራት መካከል ግንኙነት ቢኖርም በበቂ ደረጃ ተሳስረዋል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።
ግንኙነቱ መተማመን ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በጋራ ጉዳዮች ላይ መተማመንን ማጽናት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆይሴ ባንዳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤አፍሪካ ለመበልጸግ የሚያስችል የተፈጥሮ ጸጋ ቢኖራትም ኃብቱን አልምቶ መጠቀም ላይ ግን ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ያሉ ዕድሎችን በመጠቀም ለተተኪው ትውልድ ሥራ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሴቶችን ማሳተፍም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።