ቀጥታ፡

የዲጂታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው- ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ  ዜጋን ለማፍራት በተሰጠው ትኩረት የዲጂታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ  የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር  በ4ኛው ዙር ሰመር ካምፕ በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶችን አስመርቋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የሠላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፣የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዲጂታል ዘመን ወቅቱን የዋጀ በክህሎት መር እውቀት የሠለጠነ ዜጋን ማፍራት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሳይበር ደህንነት እና ዘመኑ የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ እውቀት የታጠቁ ወጣቶችን በተከታታይ የማሰልጠንና የማሰማራት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።


 

በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት በሰው ኃብት ልማት በተለይ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። 

የሳይበር ጥቃትን በብቃት የሚከላከልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ህልምን የሚያሳካ የዲጂታል አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በዲጂታል ዘርፉ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል እያደረገች ላለው ሽግግር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው ብለዋል። 


 

የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ዋና ዓላማ በዘርፉ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎት በማሳደግ እና በዘርፉ ለሀገር የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ወቅቱን የሚመጥን ብቁ፤ ዕውቀት እና ክህሎት ያለው  የሰው ኃይል ለማፍራት የሳይበር ታለንት ስልጠና አጋዥ መሆኑን  ጠቁመዋል።  

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስር በመፍጠር እና በተቋሙ የሚሰሩ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች እውቅና እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የፈጠራ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዝ የሥራ ፈጣሪዎች አቅም ማጎልበቻ ማዕከል ከፍቶ ወደ ስራ ማስገባቱንም ገልጸዋል።

በዚህም በሰመር ካምፕ የፈጠራ ስራ ያላቸው ታዳጊዎች በማዕከሉ ውስጥ የፈጠራ ስራቸውን ማስፋትና ወደ ገበያ የሚያቀርቡበትን ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።  

በሰመር ካምፑ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች በበኩላቸው በቆይታቸው የተለያዩ ክህሎቶችን ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ ሀገራቸውን በዲጂታል ዘርፎች ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።


 

ወጣት አሌክሳንደር ሳሙኤል  የኢ-ለርኒንግ ስርዓት ማበልጸጉን በማንሳት፥ የጀመረው ሥራ የትምህርት ስርዓቱን በዲጂታል ለማሳለጥ ዓላማ  ያለው ነው ብሏል።


 

ሌላው ወጣት ኬና ቶልቻ በበኩሉ በቆይታው በኤሮስፔስ ዘርፍ ስልጠና መውሰዱን በመግለፅ፥ በድሮን ኦፕሬሽን ላይ እውቀት መቅሰሙን ጠቁሟል።


 

ወጣት ባስሌል መስፍን በበኩሉ በሶፍትዌር ማበልፀግ ስልጠና  እንደወሰደ ጠቅሶ፥ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የህዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀም የሚያሳልጥ መተግበሪያ መስራታቸውን ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም