ቀጥታ፡

የመከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉአላዊነት  የማስከበር  ኃላፊነቱን  በላቀ ብቃት እየተወጣ  ነው

ድሬዳዋ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- የመከላከያ ሰራዊት  የሀገርን ሉአላዊነት የማስከበር  ኃላፊነቱን በአኩሪ ጀግንነትና  በላቀ ብቃት  እየተወጣ መሆኑን  የኢፌዴሪ አየር ኃይል የሶስተኛ አየር ምድብ  ስታፍ አስተባባሪ ምክትል አዛዥ  ኮሎኔል ዱላ ደበጭ  አስታወቁ። 

በድሬዳዋ የሶስተኛው አየር ምድብ አመራሮች እና አባላት 118ኛውን   የሠራዊት ቀን " የማትደፈር ሀገር፣ የማይበገር ሠራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ማክበር ጀምረዋል።

ቀኑ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በልማት ተግባራት ፣ በፓናል ውይይት እና በፅዳት ስራዎች  ነው የተከበረው። 


 

በዚህ ወቅት የሶስተኛው አየር ምድብ ስታፍ አስተባባሪ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ዱላ ደበጭ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሰራዊት ቀን የእርስ በእርስ ትስስርና አንድነትን ይበልጥ በሚያፀኑ እና በሚያልቁ  ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

የዘንድሮው በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበትና የባሕር በር የማግኘት ህጋዊና ተፈጥሯዊ መብት የዜጎች ሁሉ አጀንዳ በሆነበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።


 

ሠራዊቱ የሀገርን ሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅሞች የማስከበር ኃላፊነቱን በታላቅ ብቃት፣ በአኩሪ ጀግንነትና ቁርጠኝነት  እየተወጣ  እንደሚገኝ ኮሎኔሉ አስታውቀዋል።

በቀጣይም ሀገራችንን ከታሪካዊ ጠላቶቻችንና ባንዳዎች በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቁን ተልእኮ በላቀ ብቃት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የሶስተኛ አየር ምድብ የሰራዊት ስነምግባር ዋና ክፍል ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ጌታቸው ማሞ በበኩላቸው ፤ በምድቡ መከበር የጀመረው  በዓል  ሰራዊቱ አገራዊ ተልዕኮውን የመወጣት ዝግጁነቱን ከማጠናከር ባሻገር በማህበራዊ ልማት ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።


 

ሰራዊቱ ለየትኛውም ፈተና ሳይበገር የአገርን ዳር ድንበርና ሉአላዊነት በአስተማማኝ መንገድ እየጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሎኔል ጌታቸው፤ ሰራዊቱ በሁሉም መስክ ራሱን በማዘመን የሀገርን ሉአላዊነት የማስከበር፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተልዕኮውን በላቀ  ብቃት መወጣቱን  ቀጥሏል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም