በመደመር እሳቤ ሀገር በቀል እውቀቶችንና የአብሮነት መገለጫ እሴቶችን በማካበት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር እሳቤ ሀገር በቀል እውቀቶችንና የአብሮነት መገለጫ እሴቶችን በማካበት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል- ምሁራን
ዲላ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በመደመር እሳቤ ሀገር በቀል እውቀቶችንና የአብሮነት መገለጫ እሴቶችን በማካበት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሰላም ሚኒስቴርና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር "ስለ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይት በዲላ ከተማ አካሄዷል።
መድረኩ "ሰላም ለኢትዮጵያ ማንሰራራት" በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን በባህላዊ እሴቶች ዙሪያ ምሁራን የውይይት መነሻ ፅሁፎችን አቅርበዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በብዝሃ ባህል የተዋበች ለሰላም እሴት ግንባታ መሰረት የጣሉ ባህሎችና ልማዶች መገኛ መሆኗን አጽንኦት ሰጥተዋል።
"ማህበረ ባህላዊ እሴቶች ለአንድነታችን ያላቸው ሚና" በሚል መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት በአውስትራሊያ የዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን፤ ኢትዮጵያ በብዝሃ ባህል የተዋበች ለሰላም እሴት ግንባታ መሰረት የጣሉ ባህሎችና ልማዶች ያሏት ድንቅ ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
በተለይ አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰላም ከታች የሚጀመር የህዝቦች ትስስር ውጤት መሆኑን አለመገንዘብ በሀገር መንግስት ግንባታ ላይ ጫና ማሳደሩን አስረድተዋል።
የመደመር መንግስት ሀገራዊ ወረቶችን ደምሮ ለላቀ ልማትና ሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት እያኖረ መሆኑን ገልጸው ሀገር በቀልና የካበቱ የሰላም ግንባታ አቅሞችንና የአብሮነት መገለጫ እሴቶችን በማካበት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለው ሰላም የህዝቦችን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ ጸጋዎችን እንድንጠቅም አቅም ፈጥሯል ያሉት ደግሞ "በሰላምና ልማት ቁርኝት" ላይ ሃሳብ ያቀረቡት በክልሉ ምክትል ርእስ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) ናቸው።
በክልሉ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለግብርና ልማት በማዋል የቡና፣ የቅመማ ቅመምና የቅባት እህሎች ከምግብ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ለዚህም በክልሉ የሚገኙ ብዝሃ ባህልና የሰላም እሴቶች ድርሻቸው የጎላ መሆኑን አንስተው ይህንንም በማጠናከር ብልጽግናን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ያለው ፋይዳ" በሚል ርዕስ ሀሳብ ያቀረቡት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁኔታዎች ክትትል ዳይሬክተር ጄኔራል ዘሩባቤል ጌታቸው (ዶ/ር) በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ ትስስር ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በውሃ፣ በኃይል ልማትና በግብርና ምርቶች አቅርቦት ድርሻዋ የጎላ መሆኑን አንስተው ይህንኑ የሚመጥን የመሪነት ሚናን ለማጠናከር የውስጥ አቅም ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
በቀጣናው ያለውን የምጣኔ ሃብት ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ለማጎልበት የኢትዮጵያ ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።