ሰላምን ለማጽናት እንሰራለን - የወልዲያ ከተማ ነጋዴዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን ለማጽናት እንሰራለን - የወልዲያ ከተማ ነጋዴዎች
ወልድያ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፡- በሰላም ወጥተን ለመግባትና ሰርተን ለመኖር የሚስፈልገን ሰላም በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጥል እንሰራለን ሲሉ የወልዲያ ከተማ የንግድ ማሕበረሰብ አባላት ገለጹ።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ከንግዱ ማሕበረሰብ ጋር "ሰላም ለሁሉም! ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ተወያይተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊ የንግዱ ማሕበረሰብ አባላት መካከል አቶ ቢሰጠኝ አዲሱ በወቅቱ እንዳሉት፤ ነጋዴው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመስራትና ቤተሰቡን ለማስተዳደር የሰላም መኖር ወሳኝ ነው።
የፅንፈኛው ቡድን የጥፋት ተላላኪዎች ነጋዴውንና አርሶ አደሩን በመዝረፍ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በማውደምና ሰውን በማገት ሃብትና ቁስ በማካበት ችግር ሲፈጥሩብን ቆይተዋል ብለዋል።
የጥፋት ተላላኪዎችን እኩይ ሴራ ለማምከን ከመንግስት ጎን ተሰልፈን በቁርጠኝነት በመስራት ለውጥ አምጥተናል ይህንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል።
ችግርን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የውይይት መድረክ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ጫኔ ዓለሙ ናቸው።
ጽንፈኛው ቡድን በፈጠረው ችግር ተንቀሳቅሰው ለመስራትና ነግደው ለማትረፍ ሲቸገሩ እንደቆዩ አስታውሰው፤ በቀጣይም የሚያስፈልገን ሰላም በዘላቂነት ፀንቶ እንዲቀጥል ተሳትፏችንን ይበልጥ እናጠናክራለን ሲሉ ገልጸዋል።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ፤ ጽንፈኛ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የንግዱ ማህበረሰብ እገዛ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊታችን ለመላው ሕዝባችን ሰላምና ደህንነት ውድ ህይወቱን እየሠጠ ነው ያሉት ደግሞ በ11ኛ ዕዝ የሠራዊት ሥነ- ልቦና ግንባታ ኃላፊ ኮሎኔል አክሊሉ አበበ ናቸው።
ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ጽንፈኛውን እያሳደደና እየደመሰሰ ከአካባቢው እያጸዳ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ይህንኑ ተግባር ዳር በማድረስ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረትም የወልዲያና አካባቢው የንግዱ ማሕበረሰብ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።