ቀጥታ፡

ማህበሩ ለደቡብ ወሎ ዞን ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ፣ የመድሃኒትና የአምቡላስ ድጋፍ አደረገ

 ደሴና ገንዳ ውሃ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)-  የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለደቡብ ወሎ ዞን ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ፣ የመድሃኒትና የአምቡላስ ድጋፍ አደረገ።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን በድጋፍ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት በዞኑ የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻልና ግብዓት በማሟላት የሕክምና አገልግሎቱን ለማሻሻል እየተሰራ ነው።


 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዛሬ ያደረገው ድጋፍም የጤናውን ዘርፍ በማጠናከር ፈጣን፣ ጥራቱን የጠበቀ ተደራሽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፣ ማህበሩ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የሚስተዋለውን የሕክምና ቁሳቁስና መድሃኒት እጥረት ለማቃለል የሚያስችል ነው።


 

በተለይም የሁለቱ አምቡላንሶች ድጋፍም የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማገዝ የሚያስችሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።


 

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ቸኮል በበኩላቸው፣ ማህበሩ ዘርፉን በመደገፍ ሕብረተሰቡ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ እያገዘ ነው።


 

ዛሬ ለደቡብ ወሎ ዞን ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሁለት አምቡላንሶች፣ ማይክሮስኮፕ፣ ኬሚስትሪ ማሽን፣ አልትራሳውንድ፣ የአተነፋፈስ መቆጣጠሪያ ማሽንና ሌሎች መሳሪያዎች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

በተያያዘ ዜናም የመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ከአጋር ድርጅት ማግኘቱን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አዲሱ ገልጸዋል።


 

ከመድሃኒትና የህክምና መሳሪያው በተጨማሪም ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤትና መታጠቢያ ቤት በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል። 

የምእራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ዮሴፍ ጉርባ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ ለነዋሪዎችና  ስደተኞች የሚሰጠውን ህክምና ለማሻሻል የሚያስቸል ነው ብለዋል።

በቀጣይም ለጤናው ዘርፍ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም