ቀጥታ፡

በክልሉ በተለያየ ምክንያት ምርታማነቱን ያጣ የእርሻ መሬትን በማከም ወደ ልማት እየተመለሰ ነው

ሀዋሳ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል በተለያየ ምክንያት ምርታማነቱን ያጣ የእርሻ መሬትን በማከም ወደ ልማት የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ባንጉ በቀለ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።


 

በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጥሮ ሀብታቸው ተመናምኖ ምርታማነቱን ያጣ አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከምና በተፋሰስ በማልማት ወደ እርሻ መሬት እንዲለወጡ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

ተዳፋት የበዛበትን አካባቢና ተራራማ መሬትን ህዝቡን በማስተባበር የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በመሰራቱ ወደ እርሻ ማሳነት መለወጣቸውን ተናግረዋል።


 

በበንሳ፣ ሀገረ ሰላም፣ ጠጢቻና ሌሎች ደጋማ አካባቢዎች የመሬቱን አሲዳማነት ለማከም ከ80 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ በማቅረብ መሬቱን ማከም እንደተቻለም ገልጸዋል።

በክልሉ ደቡባዊ ሲዳማ ዞን ሀገረ ሰላም ወረዳ ልዩ ኡዱሜ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ፋንታዬ ፉጡኔ እንዳሉት የእርሻ ማሳቸው ተዳፋታማ በመሆኑ በናዳና በመሬት መንሸራተት ሳቢያ ምርታማነቱን አጥቶ ነበር።


 

ማሳውን በተፋሰስ ልማት ጠረጴዛማ እርከን ስራ መልሶ እንዲያገግም በማድረግና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም መልሰው ለእርሻ ስራ እንዲውል ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

መሬታቸው በመራቆቱና አሲዳማ በመሆኑ ምክንያት ምርቱ እየቀነሰ በመምጣቱ የሚያመርቱት ምርት ለቤተሰብ እንኳን ሊበቃ እንዳልቻለ ያስታወሱት ደግሞ የወረዳው አለቃ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አየለ ጋልፈቶ ናቸው።


 

አሁን ግን ከአፈር ማዳበሪያው በተጨማሪ ኖራ በመጠቀም ያለሙት ማሳ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ከበፊቱ የተሻለ ምርት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲዳማ ክልል በተያዘው የምርት ዘመን 160 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም