የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየታዩ ነው- ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየታዩ ነው- ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዳማ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- የትራንስፖርት ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየታዩ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ( ዶ/ር) ገለጹ።
በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው በፌዴራል ተቋማት የአደረጃጀት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ( ዶ/ር)፤ በበጀት ዓመቱ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት መሰረት የሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉም ለሀገር ማንሰራራት ትልቅ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የአሰራር ለውጦች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የአፈር ማዳበሪያን በማጓጓዝ የትራንስፖርት ዘርፉ ትልቅ አሻራ እያኖረ መሆኑን አንስተው የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የአሽከርካሪዎችን የሙያዊ ብቃት የማጎልበት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ማስቀረትን ጨምሮ ሌሎችም ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።
የትራንስፖርት ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አመራር እና አባላት በዘርፉ የተገኘው ውጤት የበለጠ እንዲጠናከር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታና በፓርቲው የትራንስፖርት ወረዳ የፖለቲካ ዘርፍ ሰብሳቢ አቶ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው፤ ስልጠናው የተዘጋጀው የፓርቲው አመራርና አባላት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖራቸው ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
ስልጠናው ከመደመር እሳቤ እስከ መደመር መንግስት መፅሐፍ ላይ በማተኮር ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይህም የፓርቲው አመራር እና አባላት የፓርቲውን የአሰራር ደንቦችና መመሪያዎች ተገንዝበው እንዲፈጽሙ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።