ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጊዜና ገንዘባችንን እንድንቆጥብ አስችሎናል-ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጊዜና ገንዘባችንን እንድንቆጥብ አስችሎናል-ተገልጋዮች
ወላይታ ሶዶ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር እየሰጠ ያለው ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጊዜና ወጪያቸውን እንደቆጠበላቸው ተገልጋዮች ተናገሩ።
ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነው አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋይን እንግልት ከመቀነሱም ባሻገር የህገወጥ ደላሎችን ማዋከብ እንዳስቀረላቸው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተገልጋዮች ተናግረዋል።
ከተገልጋዮች መካከል አቶ አማኑኤል ቡናሮ ከዚህ ቀደም ጉዳይ ለማስፈጸም ይመላለሱ እንደነበር አስታውሰዋል ።
አሁን ላይ ይህን ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው ከወረቀት ንክኪ ነፃ አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳያቸውን በአፋጣኝ እንዲጨርሱ ማገዙን ተናግረዋል።
ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ዳንኤል ዝናቡ በበኩላቸው የማዘጋጃ ቤቱ የኦንላይን አገልግሎት መጉላላትና ብልሹ አሰራርን ያስቀረ ነው ብለዋል።
በተለይም ጉዳይ እናስጨርሳለን በሚል ሰበብ የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ደላሎች የሚያደርሱትን ማዋከብም ማስቀረቱን አስረድተዋል።
ከወረቀት ንክኪ ነፃ የማዘጋጃ ቤታዊ የኦንላይን አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ማሳደግ እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሻለ ታደሰ ናቸው።
አገልግሎቱ በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማህበረሰቡን ጊዜ በመቆጠብ እንግልትን ከማስቀረት ባለፈ የማዘጋጃ ቤቱን ገቢ እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ህዝቡ በአንድ መስኮት የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ ከፍተኛ ድርሻ መወጣቱንም አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንዳሉት በክልሉ የማዘጋጃ ቤቶች አገልግሎት የተወሳሰበ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚነሱበት ነበር።
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም የማዘጋጃ ቤቶችን አገልግሎት ለማዘመን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ለሆነ የኦንላይን አገልግሎት ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
ተግባሩንም እውን ለማድረግ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት በሶስት ከተሞች የማዘጋጃ ቤቶች የኦንላይን አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል።
ስራው በተጀመረባቸው ከተሞችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማየት እንደተቻለ ጠቁመው ስራውን በክልሉ ባሉ ሁሉም ከተሞች ለማስፋት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የኦንላይን አገልግሎትን መስከረም 23 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ስራ ማስጀመራቸው ይታወሳል።