ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ ለታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማነት የክትትልና ድጋፍ ስራው ይጠናከራል

ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በጋምቤላ ክልል በበጀት ዓመቱ ለታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማነት የክትትልና ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላከተ።

የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የ2018 በጀት አመት 1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም በመስክና በመድረክ ገምግመዋል፡፡ 


 

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ መሠረት ማቲዎስ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ በበጀት ዓመቱ ለታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማነት የክትትልና ድጋፍ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴዎቹ አማካኝነት በአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በአግባቡ መተግበራቸውን እየገመገመ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡


 

በዚህም በበጀት ዓመቱ በአንደኛ ሩብ ዓመት በማህበራዊ߹ በኢኮኖሚያዊና በመልካም አስተዳደር የልማት መስኮች  አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን የቋሚ ኮሚቴው የመስክና የመድረክ ግምገማ ያሳያል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ክልሉ ያለውን ውስን በጀት ለታለመለት ዓላማ በማዋል የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምክር ቤቱ የተጀመረው የክትትልና የቁጥጥር ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም በሚኖሩበትና በሚሰሩበት አካባቢ ያለው ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ ረገድ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም አፈ-ጉባኤዋ አሳስበዋል፡፡ 

በክልሉ ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኡሞድ ኡቹዶ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ከማድረግ አንጻር አበረታች ውጤት መታየቱን ገልጸዋል፡፡


 

በጤናው ዘርፍ የመድሃኒትና የህክምና ግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል አገልግሎቱን ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ከማስፈን አንጻር አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የጠቀሱት ደግሞ በክልሉ ምክር ቤት የህግና ፍትህ ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡፖራ አጉዋ ናቸው፡፡


 

በመሆኑም አሁን ላይ በክልሉ እየታየ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ይበልጥ  አጠናክሮ ለማስቀጠል ቋሚ ኮሚቴው የጀመረውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም