ቀጥታ፡

በክህሎት መር የሥራ ዕድል በተፈጠረው ምቹ መደላድል ሰፊ  የስራ እድሎች ተፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በክህሎት መር የሥራ ዕድል የተፈጠረው ምቹ መደላድል አማራጭ የስራ እድሎች መስፋታቸውን  የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ የስራ መስኮች በአማራጭነት እየተስፋፉ ናቸው።

ግብርና፣ ቱሪዝም፣ የኮንስትራክሽን እና ሌሎች መስኮች ለስራ እድል ፈጠራ አቅም እየፈጠሩ መሆናቸውን ነው ያነሱት። 


 

እነዚህን የስራ ዕድሎች በመጠቀም የሀገርን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሀይል እና ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ማጎልበት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። 

በዚህም ዜጎች ያካበቱትን ክህሎት ወደ ስራ መቀየር እንዳለባቸው አመልክተው፤ የዲጂታል አማራጮች እንዲሁም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ውጤታማ የሚሆኑበትን ምቹ መደላድል ፈጥሯል ብለዋል።


 

ዜጎች በክህሎት መር የሥራ ዕድል የተፈጠረውን መልካም ሁኔታ በመጠቀም ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በክህሎትና በፈጠራ ሥራ የተካነ የሰው ሀይል በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

ኢኒስቲትዩቱ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ 11 አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞችን ቀርጾ  ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ከስልጠና ፕሮግራሞቹም መካከል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ሳይበር ሴክዩሪቲ፣ ባዮ ሜዲካል ቴክኖሎጂ፣ ፕላስቲክ ቴክኖሎጂ እና ኢንቴሪየር ዲዛይንን ለማሳያነት አንስተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ በየክልሎች ያሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በየአካባቢያቸው ያሉ ጸጋዎችን ታሳቢ ያደረጉ  የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አይነቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለማስቻል ኢንስቲትዩቱ የዘርፉ ተዋናዮች አቅም ግንባታ ተግባር እያከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም