በዞኑ የግብር ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ልማት ላይ ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የግብር ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ልማት ላይ ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል
ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በምሥራቅ ጎጃም ዞን ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን የግብር ገቢ አሟጦ በመሰበሰብ ልማት ላይ ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ገለጸ።
በበጀት ዓመቱ በዞኑ ከሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን መምሪያው አስታውቋል።
የመምሪያው ሃላፊ ጥሩምርት አለልኝ፤ በዞኑ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠል በተያዘው የበጀት ዓመት ከሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ በሩብ ዓመቱ ከሰባት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
ከመደበኛ እና ከከተማ አገልግሎት የተሰበሰበው ይሄው ገቢም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ275 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አውስተዋል።
ብልጫው የተገኘውም ገቢውን ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
በደጀን ከተማ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ስዩም ተዋቸው ፤ ግብርን መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑንና መብትን ለመጠየቅ የሚያስችል የስልጣኔ ምልክት ነው ብለዋል።
ይህን በመገንዘብም ከተሰማሩበት የአልባሳት ንግድ ስራ ዘንድሮ ከ30 ሺህ ብር በላይ የመንግስት ግብርን በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል።
በአነደድ ወረዳ የአንበር ከተማ ነዋሪ አቶ ያረጋል ዳምጤ በበኩላቸው፤ ልማትና እድገትን ማረጋገጥ የሚቻለው ተገቢውን ግብር ለመንግስት በመክፈል መሆኑን ገልጸዋል።
እኔም በእህል ንግድ ስራ በመሰማራት ካገኘሁት ገቢም ዘንድሮ ከ45 ሺህ ብር በላይ ግብር በወቅቱ ከፍያለሁ ብለዋል።
ከገቢዎች መምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2017 የበጀት ዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ለልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ማዋል ተችሏል።