የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው
ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ) ፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የድሬዳዋን የጎርፍ ስጋት በመቀነስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር አካባቢ ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ።
በአስተዳደሩ ባለፈው ክረምት ለተተከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
የባለስልጣኑ የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች የጎርፍ ስጋትን በመቀነስ በከተማዋ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው።
ባለፈው ዓመት በአስተዳደሩ ከተተከሉት ችግኞች 50 በመቶዎቹ ለገጠር ማህበረሰብ ተጨማሪ ገቢን የሚፈጥሩ እና የከተማ የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ፍራፍሬዎች ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም ለኮሪደር ልማቱ ስኬት አስተዋጽኦ ያላቸው የጥላና የውበት ችግኞች ተተክለው ከተማዋን ውብና አረንጓዴ እንዲሁም ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በገጠር የተተከሉት የፍራፍሬ ችግኞች ተጨማሪ ገቢ ከመፍጠር ባሻገር የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የአመጋገብ ስርዓትን እየለወጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በተለይ ከተጎራባች የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች እና ከሲቲ ዞን ጋር በመቀናጀት በአዋሳኝ ተፋሰሶች ላይ የተተከሉት ችግኞች መሠረታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
ለችግኞቹ በባለቤትነት እንክብካቤ በመደረጉም የአካባቢውን ስነ-ምህዳር በመለወጥ የደን ሃብት ሽፋንን ማሳደግ አስችለዋል ብለዋል።
በአስተዳደሩ ተቋማት ኃላፊነት ወስደው ለችግኞች እንክብካቤ በማድረጋቸው የተተከሉት በሙሉ በመፅደቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በቀላሉ በማምረት የጀመርነውን የከተማ ግብርና ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል አስችሎናል ያሉት ደግሞ የአሰገደች የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት መኮንን ናቸው።
ማዕከሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከልና ተንከባክቦ በማፅደቅ ከራሱ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢጀ አነኒ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ኡመር መሐመድ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከሏቸው ችግኞች ማሳቸውን ከጎርፍ ለመከላከልና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።
ከደረሰው የፓፓያ ምርት በየአመቱ ከሰላሳ ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙም አክለዋል።