ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማት ስራ የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለዜጎች ምቹ የአኗኗር ዘይቤ እየፈጠረ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማት ስራ የከተማን ገጽታ ከመቀየር ተሻግሮ ለዜጎች የስራ ዕድል እና ምቹ የአኗኗር ዘይቤ እየፈጠረ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የሳር ቤት-ጀርመን አደባባይ-ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኮሪደር ልማት ስራው ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ገጽታ እና ውበት መስጠቱን ገልጸዋል።

ስራው የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ፣ መንገዶችን ለእግረኞች ምቹ በማድረግና የተገነቡት ሱቆች ለዜጎች የስራ ዕድልን የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኮሪደሩ የሚገኙ ከ20 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ስፖርቱን ለማሳደግና ትውልድን ለመቅረጽ የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።


 

የከተማው ነዋሪ ምቹ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተል መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ብልጽግና ፓርቲ ከታች ጀምሮ በትውልድ ላይ እየሰራ መሆኑ በግልጽ የታየበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ስራ መንገድ ከመገንባትና ከማስዋብ ባሻገር የከተማን ገጽታ የመቀየር ግብ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ከአዲስ አበባ ባለፈ በኢትዮጵያ የገጠር ክፍል እየሰፋ እንደሚገኝም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም