ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማቱ  የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እና ቃልን በተግባር የቀየረ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):-የሳር ቤት - ጀርመን አደባባይ - ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት አካታችና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ቃልን በተግባር የቀየረ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የሳር ቤት - ጀርመን አደባባይ - ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን በማስመልከት ባደረጉት ገለጻ፤ ሳር ቤት - ጀርመን አደባባይ - ጋርመንት እና ፉሪ  የኮሪደር ልማት በከተማዋ በሁለተኛው ዙር ከተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች መካከል አንዱ ነው። 

የኮሪደር ልማቱ ከመንገድ መሰረተ ልማት በተጨማሪ በርካታ የከተማ መልሶ ማልማት ስራዎች የተካተቱበት  መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

በኮሪደር ልማቱ  ዜጎች  የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን አመልክተው፤ ለዚህም 1ሺህ 100 ሱቆች የኮሪደር ልማት አካል ሆነው መገንባታቸውን አብራርተዋል። 

ይህም ልማቱ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል። 


 

በዋናነት ለአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል 20 የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችና 20 የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች መገንባታቸውን ገልጸዋል።

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አካል የሆኑና ደረጃቸውን የጠበቁ 40 የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታን ጨምሮ አምስት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች በኮሪደር ልማቱ ማካተት ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም