ቀጥታ፡

የሰብል ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ‎‎የእርሻ ውል አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው

ባሕርዳር ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የሰብል ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው  ‎‎የእርሻ ውል (ኮንትራት ፋርሚንግ) አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና  በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ  በትብብር  የተዘጋጀ  የኮንትራት ፋርሚንግ  የ(እርሻ ውል)  ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

‎‎የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፥  ግብርናውን ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ውል ስምምነት ፋይዳው የጎላ ነው።

‎‎የእርሻ ውል " ኮንትራት ፋርሚንግ" ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እንደሀገር ራሱን የቻለ አዋጅ ወጥቶለት በህጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አውስተዋል።

‎‎‎አዋጁም በአምራች አርሶ አደሮችና በተረካቢ ባለሃብቶች መካከል የፋይናንስ፣ የግብዓት አቅርቦትና የዕውቀት መደጋገፍ እንዲኖር በማድረግ በዓይነትና በጥራት የተሻለ ምርት ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

‎‎አርሶ አደሩ ከባለሃብቱ ያገኘውን ድጋፍ ተጠቅሞ ምርታማነትን በማሳደግ ለወጭ ንግድና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ምርቶች በብዛትና በጥራት በማምረት እንዲያቀርብ ማስቻሉን አስረድተዋል።

የሰብል ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ  አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑንም  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር)  በበኩላቸው፤  ግብርናውን ለማዘመንና ትራንስፎርም ለማድረግ የእርሻ ውል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል። 


 

‎‎በቀጣይ አምስት ዓመታት በኩታ ገጠምና ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን  በመተግበር ምርታማነትን በማሳደግ ለሀገር እድገት ለማዋል የእርሻ ስምምነቱ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።

በክልሉ  በ2017/2018 የምርት ዘመን   781 ሺህ ሄክታር መሬት በእርሻ ውል ስምምነት በተለያዩ ሰብል  መልማቱን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ናቸው። 


 

‎‎የውል ስምምነቱ የተፈጸመውም በ631 አስመራች ባለሃብቶችና ከ280 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም  ሰሊጥ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተርን ጨምሮ ሰባት ገበያ ተኮር ሰብሎች ለምተዋል ብለዋል።

‎‎የአዊቱ አስመጭና ላኪ ድርጅት ተወካይ አቶ መሰረት ልጃለም፤  የሚፈልጉትን ምርት በጥራትና በብዛት ለማስመረት ከሁለት ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ጋር ውል ገብተው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።


 

‎‎የመድረኩ ተሳታፊ አርሶ አደር መለሰ መሃባው በበኩላቸው፤  ውል ገብቼ ማምረት ከጀመርኩ ወዲህ የብድር፣ የግብአትና ሌሎች ድጋፎችን በማግኘቴ የተሻለ ማምረት ችያለሁ ብለዋል። 


 

‎በመድረኩ ‎‎‎ላይ  የፌዴራልና የክልሉ የዘርፉ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም