ቀጥታ፡

ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ የጋራ ርብርብን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):-ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ከግብ ለማድረስ የጋራ ርብርብን ማጠናከር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ኢትዮጵያ በህዝብ ትብብር እውን የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ማስመረቋን አስታውሰዋል። 

በተጨማሪም የጋዝ ፋብሪካ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባትም ስራዎች መጀመራቸውን አንስተዋል። 

ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ይህንንም በአጭር ጊዜ እውን ማድረግ እንችላለን ብለዋል።

ይህንንም ለማሳካት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አሁን ላይ እየታየ ያለውን የስራ መንፈስ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህም የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ እንደሚቻል አመልክተዋል።

በግብርናው ዘርፍ በስንዴ እንዲሁም በሩዝ ምርታማነት ላይ የተከናወኑ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በእንቁላል፣ በማር፣ በስጋ እና በዓሳ ሀብት ምርት ላይ የተገኙ ውጤቶች መፍጠር የምንችለውን አሳይተውናል ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከማድረግ ባለፈ በአግሮ ፕሮሰሲንግ በማስተሳሰር ከዚህ ቀደም ያልታዩ ውጤቶች እየተገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋ ብሩህ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አለመግባባቶችን በመነጋገር መፍታት እንደሚገባ አመልክተው፤ ለዚህም የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

በመነጋገር እና በመመካከር ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስተላለፍ እንደሚቻል ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ገጽታ በጉልህ እየቀየሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቅሞችን በመደመር በፈጠራ በመታገዝ ስራዎችን በፍጥነት ለማከናወን የተጀመሩ ጥረቶችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም