የአፍሪካውያንን የጋራ ግቦች ለማሳካት በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን ይገባል -የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካውያንን የጋራ ግቦች ለማሳካት በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን ይገባል -የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካውያንን የጋራ ግቦች ለማሳካት በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማስፈን እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
11ኛው ጣና ፎረም በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።
ፎረሙ "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ስርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ሲሆን ሰላምና ደህንነት በአፍሪካ ያለበት ደረጃ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየመከረ ነው።
ዓለም ያልተጠበቁ ለውጦችን እያስተናገደች ባለበት በዚህ ወቅት አፍሪካ ለውጦችን ተቋቁሞ ለመቀጠል ምን ዓይነት ስልቶችን ገብራዊ ማድረግ አለባት የሚለው የፎረሙ ማጠንጠኛ አጀንዳ ነው።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህ ተግባራዊነት ማሳለጥና ቀጣናዊ ትብብሮችን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ከፎረሙ ግቦች መካከል ናቸው።
በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ባለው ፎረም ላይ የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ልዩ መልዕክተኞችን ጨምሮ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሁሉም መስክ የተሻለች፣ ሰላሟ የተጠበቀና የበለፀገች አፍሪካን እውን የማድረግ ግብን ያዘው አጀንዳ 2063ን ለማሳካት ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ግጭት የሌለባት እና የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አህጉርን እውን ለማድረግ የተያዙ ግቦች በሚፈለገው ደረጃ እየተሳኩ አይደለም ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ለስኬቱ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ በሁሉም አህጉራዊ ግቦች አበረታች ጅምሮች መኖራቸውን ገልጸው፥ ለላቀ ስኬት ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን በአፍሪካ ማስፈን የግድ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህ ደግሞ እንደ አህጉር በጋራ በመሆን ተግባራዊ እርምጃዎችን ልንወስድ ይገባል ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ለሚገጥሙ ችግሮች በጋራ መፍትሄዎችን ለማመላከት እንደ ጣና ፎረም ዓይነት መድረኮች ወሳኝ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
በአፍሪካ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቡርኪና ፋሶ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጣና ፎረም ተጠባባቂ የቦርድ ሊቀ መንበር ላሲና ዜርቦ እንዳሉት፤ በአፍሪካ ለሰላምና ደህንነት ችግሮች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ መስራት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ፍትህን ማረጋገጥ ፣የኢኮኖሚ በተለይም የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አንስተዋል።