ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለመዳፈር የሚሞክርን የትኛውንም አካል ሰራዊቱ አይታገስም- ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ

ደብረ ብርሃን  ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለመዳፈር የሚሞክርን የትኛውንም አካል ሰራዊቱ አይታገስም ሲሉ በሀገር መከላከያ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ ገለጹ።

"የማትደፈር ሀገር የማይበገር ሠራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ 118ኛው የሰራዊት ቀን በደብረ ብርሃን ከተማ የሰራዊቱ አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት  ተከብሯል።


 

በክብረ በዓሉ ላይ   በመገኘት ንግግር ያደረጉት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ፤ ኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶችና ባንዳዎች አሁን ላይ ህልውናዋን ለመፈታተን እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ከጥንት እስከዛሬ በጀግኞች ልጆቿ ተከብሮ የዘለቀ መሆኑን አንስተው፤  አሁንም ለክብሯና ሉአላዊነቷ የቆመ ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ መመኪያና የመጨረሻው ምሽግ ስለመሆኑ ያነሱት ሌትናል ጀነራሉ ፤ ለሀገሩ ክብርና ለሰንደቁ ሲል ወደ ኋላ የማይል ጀግና፣ ጠንካራ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚታገዝ ሰራዊት ስለመኖሩ ገልጸዋል።


 

በመሆኑም የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለመዳፈር የሚሞክርን የትኛውንም አካል ሰራዊቱ አይታገስም ሲሉ አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ፤ የሰራዊታችን ብቃትና ጀግንነት ከኢትዮጵያም ባለፈ በሌሎች ሀገሮች የተመሰከረለት በመሆኑ በዚሁ ልክ ተገቢውን ክብርና እውቅና ልንሰጠው ይገባል ብለዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸች በበኩላቸው፤  ኢትዮጵያን የሚመስል ህብረ ብሄራዊ ጠንካራ ሰራዊት መገንባቱ ለሁላችንም ኩራት ሆኗል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም