የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው
ድሬደዋ ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ አመት አዲስ ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑን የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት መገርሳ ቃሲም (ዶ/ር)ተናገሩ።
ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ድሬዳዋ የመጡት ተማሪዎችን ትራንስፖርት በማዘጋጀት ወደ ግቢ ማስገባት ጀምሯል።
የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ህብረት አባላት አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በህብረት በማስተናገድ ወደ ማደሪያ ክፍል እያስገቡ ይገኛሉ።
የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት መገርሳ ቃሲም (ዶ/ር) እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ቀዳሚ ምርጫ ያደረጉና ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የመጡ ከ4 ሺህ 670 በላይ የመጀመሪያ አመት ተማሪዎችን ነው እየተቀበለ የሚገኘው።
የተማሪዎች ቅበላው ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን ለተማሪዎች አጠቃላይ የመማር ማስተማሩን ተግባራት፣ ህግጋት፣ የዩኒቨርስቲውን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችና የተማሪዎች ስነምግባር ላይ መሠረታዊ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተግባር ተኮር ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዛሬ ወደ ዩኒቨርስቲው እየገቡ ከሚገኙት የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሸጋው ጌትነት እና ተማሪ ቢታኒያ ካሳሁን በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ የዩኒቨርስቲውን ህግና ስርአት በማክበር ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚተጉ ተናግረዋል።