የኮይሻ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለኢንዱስትሪ ተቋማት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከሚኖረው ሚና ባሻገር የይቻላል መንፈስን የሚያሳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮይሻ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለኢንዱስትሪ ተቋማት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከሚኖረው ሚና ባሻገር የይቻላል መንፈስን የሚያሳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፦ የኮይሻ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለኢንዱስትሪ ተቋማት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከሚኖረው ሚና ባሻገር የይቻላል መንፈስን የሚያሳይና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ ውይይት አካሂደዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በውይይቱ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነባራዊ ሁኔታ ሲመች ብቻ ሳይሆን በፈተና ውስጥም የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬነት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱን እንደገና ለማስጀመር የተደረገው የመጀመርያ ጉዞ አካል እንደነበሩ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ በወቅቱ ቁጭትና የእንችላለን ስሜት ይንጸባረቅ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በመሆን በቁርጠኝነት መጀመሩንና ፕሮጀክት መጀመር የሚያስችል አቅም ባልነበረበት ወቅት በፈተና ውስጥ የተጀመረ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በቆራጥ አመራር ፕሮጀክቱ ህይወት ተዘርቶበት ለእዚህ በመድረሱ መደነቃቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለኢንዱስትሪ እና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከሚኖረው ሚና ባሻገር የፖለቲካ፤ ዲፕሎማሲ እና ይቻላል መንፈስን የሚያሳይ መሆኑንና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ሚናም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡