ቀጥታ፡

የህዝብን ትስስር የሚያጠናክሩ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትኩረት ተሰጥቷል - የሰላም ሚኒስቴር

ዲላ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፦ የህዝብን ትስስር የሚያጠናክሩ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጽናት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው "ስለ ኢትዮጵያ" ሀገር አቀፍ የፓናል ውይይትና የፎቶ አውደ ርዕይ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በዚሁ ጊዜ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) የህዝብን ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

እነዚህ በጎ ባህላዊ እሴቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን ለማድረግ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ፤ በበኩላቸው "ስለ ኢትዮጵያ" ባለፋት ሁለት ምዕራፎች ሰላምና አብሮነትን በማጽናት ዙሪያ ኢትዮጵያውያን እንዲወያዩ ዕድል ፈጥሯል።


 

ይህም ለትርክት ግንባታ ድርሻው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው መድረክ የሶስተኛው ምዕራፍ ጅማሮ ነው ብለዋል።

በመድረኩም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ምሁራን ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም